ቀጥታ፡

ህገወጥ ፍልሰትን እና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦የሀገራትና የዜጎች ደህንነት ስጋት የሆኑትን ህገወጥ ፍልሰት እና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል ቅንጅታዊ ጥረትን ማጠናከር  እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው  ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክርቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስዳድር እንዳሻው ጣሰው፣ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር)፣ ሚኒስትሮች፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አመራሮች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊና ህገመንግስታዊ መብት መሆኑን ገልጸው፥ ሆኖም ህገ ወጥ የሰዎች ንግድና የማዘዋወር ወንጀል መስፋፋቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የፍልሰተኞች መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር በመሆኗ ጫናዎች እንዳሉባት አንስተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የውጭ ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል ተገቢውን ከለላና ጥበቃ እያደረገች ነው ብለዋል።

በአንፃሩ ዜጎቿ በተለያየ ምክንያት ለህገወጥ ፍልሰት እየተዳረጉና ችግር እየደረሰባቸው  መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በሰው የመነገድና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን በመጥቀስ። 

እነዚህ የወንጀል ቡድኖች በሰው ልጅ እና በሀገራት ደህንነት ስጋት መፍጠራቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያም የዚህ ስጋት ካለባቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን አንስተዋል።

በሰው የመነገድና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ዜጎቻችንን ለአስከፊ ህይወት፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት እየዳረገ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህ ወንጀል የተሰማሩ ቡድኖች በህገወጥ የሰዎች ንግድ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር እያንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የፍልሰተኞችን ሰብዓዊ መብትና የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት ማስጠበቅ የሁሉም ስራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

መደበኛ ላልሆነ ወይም ለህገወጥ ፍልሰት መነሻ የሆኑ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር ለመዘርጋት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን አፅድቃ ወደ ስራ መግባቷን ገልጸዋል። 

ሀገራዊ ህጎችን በማውጣትም በሰዎች የመነገድና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሠራች ስለመሆኗ አስረድተዋል።

የፍልሰት ጉዳይ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚጠይቅ በመሆኑ ክልሎችን እና የፈደራል ተቋማትን ያካተተ ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ተቋቁሞ በስራ ላይ ነው ብለዋል። 

በምክክር መድረኩ  በብሔራዊ  የፍልሰት ትብብር ጥምረት ፅ/ቤት አማካይነት  የኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር የህግ እና ተቋማዊ ማዕቀፎች፣ እስካሁን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ስኬቶች፣ ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የተመለከተ  የመወያያ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ከሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች ሀገራት ዜጎችን ከመመለስ፣ ለተመላሾች ተገቢውን ድጋፍ ከማድረግ እንዲሁም በኢኮኖሚ መልሶ የማቋቋም አገልግሎት ከመስጠት አንፃር በየተቋማቱ የተከናወኑ ስራዎች ቀርበዋል።

በዚህም ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም