ቀጥታ፡

የታሪክ ምሁራን ለስኬታማ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይገባቸዋል- የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦ የታሪክ ምሁራን ለስኬታማ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር " ታሪክ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት ግንባታ" በሚል መርህ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፤ የሰላም ሚኒስቴር ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሥራን በትኩረት መሥራት ዋነኛው ነው ብለዋል።


 

ስኬታማ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለማከናወንም ታሪክ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት አብራርተው፤ ለስኬቱ ከታሪክ ባለሙያዎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የሀገር ግንባታ ሥራ ከታሪክ አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ያለ ታሪክ መሠረት የሀገረ-ግንባታ ሥራ አይታሰብም ብለዋል።

የሀገር ግንባታና ታሪክ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ታሪክ ለሀገር ግንባታ ቁልፍ መሳሪያና የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ መሆኑንም ገልፀዋል።

ትውልዱ የትናንቱን ታሪክ ተረድቶ ከዛሬው ጋር እያቆራኘ እንዲሄድና እሴቱን እንዲጠብቅ የታሪክ ባለሙያዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ታሪክ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ውስጥ ትውልድን በአግባቡ እየቀረጸ ለመሄድም የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ታሪክን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለማዋል እና ትክክለኛ ግቡን እንዲመታም ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ባልተገባ መንገድ ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የሚሹ አካላትም ታሪክ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ያለውን ትልቅነት በመረዳት ለዚህ ማዋል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ስኬታማ እንዲሆንም የታሪክ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ ማኅበሩ ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል።

ሦስት ተከታታይ መጽሐፍቶችን ማሳተሙን ገልጸው፤ ታሪክ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩሉን እንዲያበረክትም እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ታሪክ የችግር ሳይሆን ሁሌም የመፍትሔው አካል ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ ሚኒስትሮች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም