ቀጥታ፡

የቡና ኤግዚቢሽን በሐዋሳና ጅማ ከተሞች ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦የቡና ላኪዎችና አቅራቢዎችን የሚያገናኝ የቡና ኤግዚቢሽን በሐዋሳና ጅማ ከተሞች ሊያካሂድ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ኤግዚቢሽን ዝግጅትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ኤግዚቢሽኑን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ኤግዚቢሽኑ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይበልጥ ለማሳደግና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ የሚመረቱ የቡና ዓይነቶችንና የጥራት ደረጃዎቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልም ብለዋል።

የቡና ኤግዚቢሽኑ በሐዋሳ ከተማ ከሰኔ 21 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲሁም በጅማ ከተማ ከሰኔ 26 እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ አክለዋል።

ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን በቡና ምርት፣ ጥራትና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የፓናል ውይይቶችም እንደሚካሄዱ ገልፀዋል።

ውይይቱ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን  ለመፍታትና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚደረግባቸውም ጠቁመዋል።

በኤግዚቢሽኑ ከ300 በላይ አቅራቢዎች ተመዝግበው የምርት ናሙና አቅርበዋልም ብለዋል።

በተጨማሪም ከ100 በላይ የቡና ላኪዎችም እንዲሁ ኤግዚቢሽኑ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም