በአውሮፓ ዋንጫው አራት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ አገራት የሚለዩባቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአውሮፓ ዋንጫው አራት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ አገራት የሚለዩባቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ 3 እና 4 ጥሎ ማለፉን የሚቀላቀሉ አገራት የሚለዩባቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
አምስት ሀገራት እስከ አሁን ወደ ጥሎ ማለፉ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።
በምድብ 4 ፈረንሳይ ከፖላንድ ከምሽቱ 1 ሰዓት 81 ሺህ 365 ተመልካች በሚያስተናግደው ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የሁለት ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ በምድቡ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች 1 ጊዜ ስታሸንፍ በተመሳሳይ 1 ጊዜ አቻ ወጥታለች። በነዚህ 2 ጨዋታዎች 1 ግብ ስታስቆጥር ምንም ግብ ግብ አላስተናገደችም።
በ4 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ፈረንሳይ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባታል። ሰማያዊዎቹ ቢሸነፉም ምርጥ ሶስተኛ ሆነው የማለፍ እድል አላቸው።
በአንጻሩ ተጋጣሚዋ ፖላንድ በምድቡ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፋ ከውድድሩ የተሰናበተች የመጀመሪያ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ሁለቱ ሀገራት በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በምድብ 4 በተመሳሳይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ኔዘርላንድ ከኦስትሪያ 74 ሺህ 475 ተመልካች በሚያስተናግደው የበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአንድ ጊዜ የአውሮፓ አሸናፊዋ ኔዘርላንድ በምድብ ሁለት ጨዋታዎቿ 4 ነጥብ በማግኘት ብዙ ጎል ባገባ በሚለው መለያ ፈረንሳይን በልጣ አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ቡድኑ 2 ግቦችን ሲያስቆጥር 1 ግብ ተቆጥሮበታል።
ኔዘርላንድ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ከምድቡ ያሳልፋታል። ብርቱካናማዎቹ ቢሸነፉም ምርጥ ሶስተኛ ሆነው የማለፍ እድል አላቸው።
ተጋጣሚዋ ኦስትሪያ ከሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች 3 ነጥብ በመያዝ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ በጨዋታዎቹ 3 ግቦችን ስታስቆጥር 2 ግቦችን አስተናግዳለች።
ኦስትሪያ ማሸነፍ ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባታል፤ አቻ ከወጣችም ምርጥ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል ይኖራታል።
ሁለቱ ሀገራት በአውሮፓ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከ4 ዓመት በፊት በተካሄደው 16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ 3 ተገናኝተው ኔዘርላንድ በሜምፊስ ዲፓይና ዴንዝል ዴምፍራይስ ግቦች 2 ለ 0 አሸንፋለች።
በተያያዘም በሂሳባዊ ስሌት አራቱም ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድል ባላቸው ምድብ 3 የሚደረጉ ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው።
የምድቡ መሪ እንግሊዝ ከስሎቬኒያ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ 50 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ራይን ኢነርጂ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
እንግሊዝ በምድቡ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ አግኝታለች፤ በጨዋታዎቹም ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር 1 ጎል አስተናግዳለች።
እንግሊዝ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባታል፤ እንግሊዝ ብትሸነፍም ምርጥ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል አላት።
ተጋጣሚዋ ስሎቬኒያ በሁለቱም ጨዋታዎች አቻ በመውጣት 2 ነጥብ ይዛ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስተናግዳለች።
ስሎቬኒያ ከምድቡ ለማለፍ የግድ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ አለባት። በአንጻሩ አቻ መውጣት ምርጥ 3ኛ ሆና የማለፍ እድሏን ያጠበዋል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በአውሮፓ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ዴንማርክ ከሰርቢያ 75 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው አሊያንዝ አሬና ስታዲየም ይጫወታሉ።
ዴንማርክ በሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች አቻ በመውጣት 2 ነጥብ ይዛ ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ ስሎቬኒያን በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የአገራት እግር ኳስ ደረጃ መለያ በልጣ 2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
2 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስተናግዳለች።
ተጋጣሚዋ ሰርቢያ በሁለቱ ጨዋታዎች 1 ነጥብ ይዛ የመጨረሻውን 4ኛ ደረጃ ይዛለች፤ 1 ግብ ስታገባ 2 ጎሎችን አስተናግዳለች።
ሰርቢያ ማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፉ በቀጥታ የማለፍ ወይም ምርጥ ሶስተኛ ሆና የማለፍ እድል ሊኖራት ይችላል። በአንጻሩ ከተሸነፈች ወይም አቻ ከወጣች ከውድድሩ የመሰናበት እድሏ ሰፊ ነው።
ሁለቱ አገራት በአውሮፓ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ጀርመን፣ስፔን፣ጣልያን፣ፖርቹጋልና ስዊዘርላንድ በአውሮፓ ዋንጫው ጥሎ ማለፍ የገቡ አገራት ናቸው።