ቀጥታ፡

የ12ኛ ክፍል ፈተናን ያለ ምንም የፀጥታ ችግር መስጠት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2016(ኢዜአ)፦ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ያለ ምንም የፀጥታ ችግር መስጠት የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የፌደራል ፖሊስ ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ፈተናው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ ተቋሙ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከክልል የትምህርት ቢሮዎችና የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ሁለት አመታት የተሰጡ የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች የነበሩ ጠንካራና አበረታች ውጤቶች እና የታዩ ክፍተቶች ቀርበው የዚህ አመት ቅድመ ዝግጅቶች ላይም ውይይት መደረጉን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም