የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ፅህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ፅህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2016(ኢዜአ)፦የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ገለፀ።
ከተመሰረተ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አዲስ አበባ ፖለቲካው መስክ የአፍሪካ ማዕከልነቷ ባሻገር በስነ ፅሁፍ ዘርፍ እንዲደገም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በዓለም ፊደል ካላቸው ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በስነ ፅሁፍ ጅማሮ ረገድም ከድንጋይ ላይ ጽሁፍ ጀምሮ ትልቅ አሻራ ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ መሆኗን ጠቅሰው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን ቦታ እና ታሪክ በሚመጠን መልኩ እንደ ሌሎች ተቋማት የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በርካታ አፍሪካዊያን የስነ ፅሁፍ ሊቃውንት በማህበሩ ጋባዥነት የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔ አሻራዎች በጎበኙበት ወቅት በኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ መደነቃቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም አፍሪካዊያን ፀሐፍትን ያሰባሰበውን የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማሀበር ጽህፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ኢትዮጵያን ይበልጥ ማስተዋወቅ እንዲቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ በአዲስ አበባ ከሊዝ ነጻ በተረከበው ቦታ የራሱን አዲስ ጽህፈት ቤት እየገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የፓን አፍሪካ ደራሲያን ማህበር ፅህፈት ቤትን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት በሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከማህበሩ አባላት መካከልም ደራሲ የምወድሽ በቀለ እና ዶክተር ታደለ ገድሌ ኢትዮጵያ በድርሰት መስክ ቀደምት የምትባልና በፓን አፍሪካዊነት መነቃቃት ቁልፍ ሚና የነበራት ሀገር እንደሆነች አንስተዋል።
በዚህም ማህበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፅህፈት ቤቱን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማህበሩ አባላቱ አዳዲስ መጻህፍት እንዲያሳትሙ ማበረታታት ቢኖርበትም ከወቅቱ የወረቀት ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ከባድ ፈተና ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የንባበብ ባህልን ለማዳበር በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡