ቀጥታ፡

መንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሀገር ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ ሰፊ ትኩረት ሰጥቷል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2016 (ኢዜአ)፦ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት  ለሀገር ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ለማሳደግ መንግስት የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከማድረግ ጀምሮ ሰፊ ትኩረት መስጠቱን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ያዘጋጀው 14ተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት "ቴክኒክና ሙያ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ ከሰኔ 15 /2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

በዛሬው እለትም የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቴክኒክና ሙያ ለዘላቂ ልማት ባላቸው ሚና ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ እንዳሉት፥ በሀገሪቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከ30 ሺህ በላይ አሰልጣኝ መምህራን መኖራቸው ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አቅም ነው።

በእነዚህ ተቋማት በየዓመቱ በመደበኛ ስልጠና ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ እንዲሁም በአጫጭር ስልጠናዎች ደግሞ እስከ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሙያ ክህሎት ቀስመው እየወጡ  ነው ብለዋል።


 

በዘርፉ የሚነሳውን የጥራት ጥያቄ ለመመለስ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው ባለፈው አንድ ዓመት የተለያዩ ህጎችን የማሻሻል ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም አገር በቀል እውቀት ትኩረት እንዳልነበረው አውስተዋል።

አሁን በተሻሻለው ፖሊሲ ዘርፉ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት የግሉ ዘርፍ፣ የመንግስትና የምርምር ተቋማት ትስስር አዋጅና የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የብቃት ማዕቀፍ ደንብ መፅደቁን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ማዕቀፉ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካለው የትምህርት ደረጃ ጋር ለማስተካከል ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

ከኢንዱስትሪዎች ጋር በትስስር እየተሰጠ ያለውን ተግባር ተኮር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለማጠናከርና የስልጠና መስኮች  ከሀገራዊ የምርትና አገልግሎት ትኩረቶች ጋር ተናበው እንዲሰጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አገሪቱን ከተረጂነት ለማላቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ የሙያና ክህሎት ባለቤት ሆኖ ስራና ገቢን እንዲፈጥር ለማስቻል እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ አገራዊ የሆነ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ሲያዘጋጅ መቆየቱን ጠቅሰው በአፍሪካ ደረጃ በሚኖሩ የክህሎት ውድድሮችና የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ላይም ተሳትፎ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የዓለም አቀፍ የክህሎት ማህበር አባል መሆኗን አንስተው ይህም በዓለም የቴክኒክና ሙያ ሳምንታትና በውድድሮች ኢትዮጵያውያን ቴክኖሎጂዎችን ይዘው እንዲቀርቡ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በውድድሩ የሚያሸንፉ ስራ ፈጣሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን የሚያስጠሩበትና በዓለምአቀፍ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ተወዳዳሪ ስርዓት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል።    

የፓናል ውይይቱ መነሻ ፅሑፍ አቅራቢ የሆኑት አበባየሁ ለማ እንዳሉት፥ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን በመፍጠር ለአገር ኢኮኖሚ ልማት የላቀ ድርሻ ያላቸው ናቸው።


 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችን ውጤታማነት በማረጋገጥ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ ተቋማት ከኢንዱስትሪው ጋር ያላቸው ትብብር መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።

በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሰጠው የስራ ላይ ስልጠና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

 

 

 

 

    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም