ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ሀገራዊ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ሀገራዊ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2016(ኢዜአ)፦ ተረጂነትን በማስቀረት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም የመቋቋም ጠንካራ ሀገራዊ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ጸጋዎች በማልማት ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ እንደምትችል ከለውጡ ወዲህ የታዩ ስኬቶች ማሳያ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ተጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ለማስቀረት መስራት እንደሚገባ የገለጹት ኮሚሽነሩ ተረጂነት ነጻነትን የሚነፍግ፣ ኢኮኖሚን የሚጎዳ እና የጠባቂነት አስተሳሰብ እንዲንሰራራ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ለመውጣትም እንደ ሀገር በአስተሳሰብ ለውጥና ተግባር ላይ በማተኮር መስራት እንደሚገባ ጠቁመው በሁሉም ዘርፎች የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተረጂነት እንድትላቀቅ የሚያስችሏት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሏት የገለጹት ኮሚሽነሩ የመንግስትና ህዝብ ቁርጠኝነት፣ ምርጥ ተሞክሮችን እና እምቅ ጸጋዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የተያዘውን ከተረጂነት የመውጣት ሀገራዊ ግብ ለማስካት በሁሉም ዘርፍ መዘጋጀትና መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም የሚቋቋም ጠንካራ ሀገራዊ ቁመና ለመፍጠር መንግስት አዲስ የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል።
ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ርዕይ ለማሳካት ተቋማት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በተለይ ለተረጂነት የሚያጋልጡ አስተሳሰቦችን ተግባራትን ለማስወገድ በሁሉም መዋቅር ያለው አመራር በአርዓያነት እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል።
ከአደጋ ስጋት መከላከል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እንደ ግብርና፣ ውሃና ኢነርጂ፣ ጤና፣ የመስኖ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራዊ እቅዱን የማሳካት ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
መንግስት ተረጂነትን የማስቀረት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን ከማሳየት ባለፈ ህዝብን አስተባብሮ ፈጣን ልማትን ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡