ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች የሀገር ውስጥ የኅክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን ጎብኝተዋል -ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች የሀገር ውስጥ የኅክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን ጎብኝተዋል -ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2016(ኢዜአ)፦ የሀገር ውስጥ የኅክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን እስካሁን ባለው ሂደት ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች መጎብኘታቸውን ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ።
ኤግዚቢሽኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቆ ለህዝብ ዕይታ ክፍት መደረጉ ይታወሳል፡፡
በዛሬው ዕለትም የጤና ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ኤግዚቢሽኑን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ ኤግዚቢሽኑ አምራቾች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እና የገበያ ዕድላቸውን ለማስፋት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኤግዚቪሽኑን ጉብኝት ላይም ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሶስት ቀናት የተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞችን ጨምሮ ከ28 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
ኤግዚቢሽኑ ላይ በኢትዮጵያ የሕክምና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲሁም የሀገር ውስጥ የኅክምና ምርትና አገልግሎቶች ለማበረታታት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።
ለስድስት ተከታታይ ቀናት ለህዝብ እይታ ክፍት ሆኖ በሚቆየው ኤግዚቢሽን ላይ ከ110 በላይ የሀገር ውስጥ የኅክምና ግብዓት አምራቾች ተሳትፈዋል።
በኤግዚቪሽኑ የኢንቨስትመንት ግንኙነት፣ የፓናል ውይይቶች እና ልዩ ልዩ ሁነቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።