ቀጥታ፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2016 (ኢዜአ)፦የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች "ጤናችን በምርታችን" የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን ጎብኝተዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ኤግዚቢሽኑን የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ሰኔ 15/2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ መክፈታቸው ይታወቃል።

"ጤናችን በምርታችን" በሚል መሪ ሃሳብ እስከ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ኤግዚቢሽኑ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተጎበኘ ይገኛል። 

በዛሬው ዕለትም የጤና ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣንን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ኤግዚቢሽኑን ጎብኝተዋል። 


 

በኢትዮጵያ የህክምና ኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲሁም የሀገር ውስጥ የህክምና ምርትና አገልግሎቶች ለህዝብ እይታ ቀርበው በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ። 

በዚሁ ኤግዚቢሽን ላይ ከ110 በላይ የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት አምራቾች እየተሳተፉ ሲሆን፥ የኢንቨስትመንት ግንኙነት፣ የፓናል ውይይቶች እና ልዩ ልዩ ሁነቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። 

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን ጤና ሚኒስቴር ከሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ማኅበራት ጋር በትብብር አዘጋጅቶታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም