በደርባን የኢትዮጵያያ ዳያስፖራ አባላት ለ“ጽዱ ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በደርባን የኢትዮጵያያ ዳያስፖራ አባላት ለ“ጽዱ ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ አፍሪካ፤ ኩዋዙሉናታል ክልል፣ ደርባንና አካባቢው የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በይፋ ያቀረቡትን ለ#ጽዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ፕሮጀክት የድጋፍ ጥሪ በመቀበል 410 ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ድጋፉ ይፋ የተደረገው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በደርባን የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በጋራ ባዘጋጁት መርሃ ግብር ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኮሚቴው ከኤምባሲው ጋር በመቀናጀት ባካሄደው እንቅስቃሴ ድጋፉን በአጠረ ጊዜ በማሰባሰብ ገቢ መደረጉን አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ኮሚቴው ገልጿል፡፡
በመርሃ ግበሩ ላይ የተገኙት በደቡብ አፍሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር)፤ ስለ#ጽዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ፕሮጀክትና የድጋፍ ጥሪ ፋይዳን በማስመልከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በደርባንና አካባቢው የሚኖሩ እንዲሁም በመላው ደቡብ አፍሪካ እና ኤምባሲው በሚሸፍናቸው ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ትስስርና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ጠንካራ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም መገለጫ በሀገር ግንባታ የልማት እንቅስቃሴዎችና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚቀርቡ ሀገራዊ የተሳትፎ ጥሪዎች ወቅታዊና ተጨባጭ ምላሽ በመስጠት ታሪካዊ አሻራቸውን በደማቅ ቀለም እያሳረፉ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡
በደርባንና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለ#ጽዱ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ላበረከቱት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የድጋፍ ማሰባሰቡ ንቅናቄ አስተባባሪ አባላትም ሀገር የሚገነባው በሀሉም ዜጎች ተጨባጭ ተሳትፎና ርብርብ መሆኑን በመገንዘብ በታላቅ ሀገራዊ ሞራልና ወኔ ላከናወኑት ስኬታማ የማስተባባር ሚና አመስግነዋል፡፡
በተመሳሳይ በመላው ደቡብ አፍሪካ እና በሌሎች ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ለ#ጽዱ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ግንባታ እና ለሌሎች ሀገራዊ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ በማድረግ ታሪካዊ አሻራቸውን የማሳረፍ ገድላቸውን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በወቅቱም በድጋፉ ለተሳተፉ የዳያስፖራ አባላትና የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የምስጋናና የአክብሮት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በመድረኩ ላይ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካታ የዳያስፖራ አባላት የተገኙ ሲሆን መተኪያ ከሌላት እናት ሀገር ኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ተጨባጭ ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ማረጋገጣቸውን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና ሀገራዊ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም የሚሲዮኑ መሪዎች፣ መላው ሠራተኞችና የዳያስፖራ አባላት 5,000 የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡