ቀጥታ፡

በአራት ክልሎች የተደረገው የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ሂደት በተሳካ መልኩ ተጠናቋል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2016(ኢዜአ)፦ በአራት ክልሎች የተደረገው የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ሂደት በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የ6ኛው ዙር ቀሪና እና የድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በተመለከተም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

በ6ኛ ዙር ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በፀጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄዱ በቀሩ ክልሎች በዛሬው እለት ምርጫ መከናወኑን ተናግረዋል።

የምርጫ ሂደቱን ነፃ፣ ገለልተኛና ተአማኒ ለማድረግ ቀደም ብሎ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው የቀሪና ድጋሚ ምርጫ ሂደቱ በአራቱ ክልሎች በ29 የምርጫ ክልሎች እና በ1 ሺህ 218 የምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱን ገልፀዋል።

በሁለት ምርጫ ጣቢያዎቾ ግን የምርጫ ቁሳቁስ ዘግይቶ በመድረሱ ለነገ ተላልፏል ብለዋል።

የምርጫ ሂደቱ ከጥዋቱ 12 ጀምሮ ድምፅ ሲሰጥ መዋሉን ገልፀው በመተከል ዞን ዳንጉር ምርጫ ጣቢያ ከነበሩ በ33 ጣቢዎች መካከል በሁለቱ ምርጫ ጣቢያዎች በቁሳቁስ መዘግየት ሳቢያ ለነገ መተላለፉን ገልፀዋል።

በአንድ ምርጫ ጣቢያ ተመሳሳይ እና ስም ያልተፃፈባቸው መታወቂዎች ተገኝተው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።

ድምፅ በተሰጠባቸው በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራ ላይ ሲሆኑ የተወሰኑት ላይ ደግሞ ወደ ምርጫ ክልል ተወስደው እንዲቆጠሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ግን በተሳካና ጥሩ በሚባል ሁኔታ መካሄዱን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም