በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል የድጋሚ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል የድጋሚ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
ጅግጅጋ፤ ሰኔ 16/2016(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል የድጋሚ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
በ2013 ዓ.ም በምርጫ ክልሉ የተካሄደው ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ የታዩ አንዳንድ ችግሮች ለማስተካከል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ከወሰነባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች አንዱ ጅግጅጋ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል ነው፡፡
በዚሁ የምርጫ ክልል በተካሄደው የድጋሚ ምርጫ የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የምርጫው ሂደት ያለምንም እንከን መከናወኑን ገልጸዋል ።
የሶማሌ ክልል የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሂርስ ዶል እንደገለጹት፤ ድጋሚ ምርጫውን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ተባብረው ሰርተዋል።
ምርጫው በሚካሄድባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ ምርጫው ነፃና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ኡመር በበኩላቸው፤ የድጋሚ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል ።
“ምርጫው በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ተዘዋውረን የተመለከትናቸው የምርጫ ጣቢያዎች ባለው እንቅስቃሴ ተረድተናል” ያሉት ኃላፊው፤ ህዝቡ የምርጫ ህጉን ተከትሎ መምረጥ መቻሉ ለምርጫው ሰላማዊነት አስተዋጽዎ ማድረጉን ተናግረዋል።
“የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሆነን ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ አግኝተነዋል። በቀጣይም ትምህርት የምንቀስምበት ነው። የህዝቡም ተሳትፎ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ አመስግነናል” ብለዋል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የጅግጅጋ ምርጫ አስተባባሪ አቶ መሀሙድ አህመድ፤ በከተማው የሚካሄደው የድጋሚ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ችግር አላጋጠመም ብለዋል።
ምርጫው እስከ መጨረሻ ስኬታማ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራታቸውን ገልጸዋል፤ ምርጫው ያለምንም ችግር በሰላም መጠናቀቅ መቻሉን አብራርተዋል።
“አብዛኛውንና ምርጫ የተካሄደባቸውን የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ያጋጠሙ ችግሮች አለመኖራቸውን አረጋግጠናል፤ ምርጫው የተሻለና ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበን የሰራንበት ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።
የኢትዮዽያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ወክለው የተወዳደሩት አቶ አብዲ መሀሙድ እንደተናገሩት፤ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዱን ተናግረዋል።