ቀጥታ፡

በደብረብርሀን ከተማ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ

ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 16/2016(ኢዜአ)፦ "በሰላማዊ ንግድ በላቀ ተወዳዳሪነት ወደ ዓለም አቀፋዊ ግብይት እንጓዝ " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የንግድ ትርኢትና ባዛር  ዛሬ በደብረብርሀን ከተማ ተከፈተ።

የንግድ ትርኢቱና ባዘሩን የተዘጋጀው  በደብረብርሀን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያና በደብረብርሀን ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ትብብር ሲሆን፤ ዝግጅቱ እስከ  ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል።


 

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ  ምክትል ሀላፊ አቶ ፋንታሁን ፈጠነ የንግድ ትርኢትና ባዛሩን ሲከፍቱ ፤  በነበረው ችግር የተቀዛቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ  ለማነቃቃት ዝግጅቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህም ነጋዴዎችንና ሸማቾችን በማቀራረብ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ያስችላል ብለዋል።

በቀጣይ የኑሮ ውድነትን ለማርገብ  በተለያዩ የክልሉ   ከተሞች የገበያ ማዕከላት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ  የሰንበት ገበያዎችም በስፋት ስራ ይጀምራሉ ሲሉም ገልጸዋል።

የደብረብርሀን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ይርጋለም ምስጋና   እንዳሉት ፤ ዝግጅቱ  የንግድ  ስራን ያነቃቃል። 


 

ከንግድ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በትብብር የተዘጋጀው የንግድ ትርኢትና ባዛሩ  በነጋዴው መካከል የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር  ምርቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል። 

የንግድ ትርኢትና ባዛር  መካሄዱ ሸማቹ ህብረተሰብ ጥራት ያለው ምርት  በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የደብረብርሀን ከተማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ  ታምሩ  በቀለ ናቸው።

ዝግጅቱ ንግድን ከማነቃቃት ባለፈ  አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከማህበረሰቡ ጋር ለማገናኘት እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

በባዛሩ የሚቀርቡት የከተማውንና በዙሪያው የሚገኙ ነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ባገናዘበ የቀረቡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በንግድ ትሪኢትና ባዛሩ የአገር ውስጥና የውጭ  ነጋዴዎች  እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶችን ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም