ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋሩ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጥቂ ኤፍራም ታምራት በ21ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ ያስቆጠራት ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል።
ይሁንና ጋናዊው የአማካይ ተጫዋች ባሲሩ ዑመር በ41ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቻ የሆነበትን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የጨዋታው ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ዩጋንዳዊውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጥቂ ሲሞን ፒተርን በ80ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን ወደ 58 ከፍ አድርጓል።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ44 ነጥብ ከነበረበት 6ኛ ደረጃ ወደ 5ኛ ከፍ ብሏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቻ መውጣቱን ተከትሎ ከተከታዩ መቻል ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ያለ ሲሆን ይህም የዋንጫ ፋክክሩን ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።
ሁለቱ ቡድኖች የቀራቸው የሁለት ሳምንት መርሐ ግብር ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሀምበሪቾ ከወላይታ ድቻ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።