በሲዳማ ክልል ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ
ሀዋሳ ፤ ሰኔ 16/ 2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት በበንሳ ወረዳ ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ የቤት ግንባታ ያስጀመረ ሲሆን፤ በጽህፈት ቤቱ አስተባባሪነት በሸበዲኖ እና አለታ ወንዶ ወረዳዎች የተገነቡ ቤቶች ርክክብ ተካሂዷል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤የህዝብን ችግር ማቃልለን ማዕከል ያደረጉ ሰው ተኮር ተግባራት የፓርቲው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል ።
በዚህ እሳቤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ባለፈው የክረምትና በጋ ወቅት ከአንድ ሺህ 300 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን በተለያዩ አካላት ተገንብተውና ታድሰው ለነዋሪዎች እንደተላለፉ አስታውሰዋል።
በዘንድሮው ክረምትም የተለያዩ አካላት በማስተባበር በችግር ውስጥ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቤቶችን የማደስና በአዲስ መልክ የመገንባት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዚህ ተግባር ቢሮዎች፣ ባለሀብቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ እድሮችና ሌሎች አቅም ያላቸው አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየሰራን ነው ብለዋል ።
ጽህፈት ቤቱ በበንሳ ወረዳ ቤታቸውን በአዲስ ለመገንባት የጀመረው ስራ ከአንድ ወር በኋላ አጠናቆና የቤት ቁሳቁስ አሟልቶ እንደሚያስረክባቸው አመልክተው፤ በተጨማሪም የወተት ላምና የእቁላል ዶሮዎችን እንደሚያበረክትላቸውም ገልጸዋል።
በጽህፈት ቤቱ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታና የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አለሙ፤ በህዝቡ ውስጥ ያሉ አደረጃጀቶች ለዴሞክራሲ ማበብም ሆነ ለልማት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሲቪል ማህበራትን በማስተባበር ባለፈው የበጋ ወቅት ሰባት የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባት መቻሉን ጠቅሰው፤ ሌሎቹንም በማሳተፍ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች በስፋት እንደሚሰሩ አስረድተዋል ።
በዚህ መንገድ በአሁኑ ክረምት አራት ቤቶች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ማህበሩ የጽህፈት ቤቱን ጥሪ በመቀበል የሁለት አቅመ ደካሞችን ቤት ገንብተን አስረክበናል ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል የግንባታ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሀሳሞ ሀሪሶ ናቸው።
ለሁለቱም ቤቶች ግንባታና ቁሳቁስ ግዢ በማካተት ከ450 ሺህ ብር በላይ ማውጣታቸውንም ጠቅሰዋል።
በማህበሩ አማካይነት ቤታቸው በአዲስ መልክ ተገንብቶላቸው ቁልፍ ተረክበው የገቡት የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቄ ጉጃሞ፤ ቤታቸውን ለማደስ አቅም በማጣት በተለይ በክረምት ወቅት ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ልጆቻቸውን እንኳ ለማስተማር ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው "ዛሬ ሕይወታችን ተቀይሯል ፈጣሪንና መንግስታችንን እናመሰግናለን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል ።