በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫው በነጻነት እና ፍትሃዊነት እየተካሄደ ነው - መራጮች እና የምርጫ ታዛቢዎች - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫው በነጻነት እና ፍትሃዊነት እየተካሄደ ነው - መራጮች እና የምርጫ ታዛቢዎች
አሶሳ ፤ ሰኔ 16/2016 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተካሄደ ያለው ስድስተኛው ቀሪ እና ድጋሚ ሀገራዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የአሶሳ ከተማ መራጮች እና የምርጫው ታዛቢዎች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በወሰነው መሰረት ዛሬ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በ29 የምርጫ ክልሎች 1ሺህ 258 የምርጫ ጣቢያዎች ከ12 ፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ 380 ዕጩዎች የሚሳተፉበት ምርጫ እንደሚካሄድ ቦርዱ ቀደም ብሎ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው፡፡
በምርጫው ድምጽ ሲሰጡ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኒማ አዙቤር እንዳሉት፤ በምርጫው ያለማንም ጫና ለመረጡት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
"ምርጫ የወደፊት ህይወታችንን የሚወስንልን ተግባራትን የሚያከናውን መሪ የምንለይበት ነው" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ በምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሂደት ደስተኛ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
አቶ አልሃሰን አልሼህ የተባሉ ሌላው ነዋሪ በበኩላቸው፤ የምርጫው ሂደት ግልጽ እና ሠላማዊ እንዲሁም ስፍራውም ለድምጽ አሰጣጥ ሂደት ፍጹም ምቹ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
"ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ በማልማት ከድህነት ያወጣኛል የምለውን መሪ መርጫለሁ" ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ወርቁ ተፈራ በበኩላቸው፤ አሁን በአሶሳ ከተማ ዋነኛ ጥያቄያቸው መካከል መሠረተ ልማት አንዱ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በምርጫው "ያለንን ውስን ሃብት እና ህዝብን በተሻለ አስተባብሮ ይሠራል ብዬ ላመንኩት የፖለቲካ ፓርቲ በነጻነት ድምጼን ሰጥቻለሁ" ብለዋል፡፡
የምርጫው ሂደት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ቁጭ ብለው ሲታዘቡ መመልከታቸውን እና የጸጥታ አስከባሪዎችም ሃላፊነታቸውን በሚገባ ሲወጡ መታዘባቸውን አስረድተዋል፡፡
"ምርጫ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብታችንን ተግባራዊ የምናደርግበት ነው" የሚሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አጠይብ ዓሊ ናቸው፡፡
ይህን ህገ መንግስታዊ መብት ደግሞ "ያለማንም ጣልቃ ገብነት ዛሬ በሰጠሁት ድምጽ ተግባራዊ አድርጌያለሁ" ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ህብረትን ወክለው ምርጫውን ሲታዘቡ የነበሩት ወይዘሮ አዳነች አስራት በበኩላቸው እንደገለጹት፤ እርሳቸው በታዘቡበት የምርጫ ጣቢያ ምርጫው እየተካሄደ የሚገኘው የምርጫ ቦርድ ህግን በተከተለ ነው፡፡
ድምጽ መስጫ ጣቢያዎችም የተዘጋጁበት ቦታ አካል ጉዳተኞች ጭምር መብታቸው በሚገባ እንዲጠቀሙ የተመቻቹ መሆናቸውን ለኢዜአ አስረድተዋል፡፡
በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ምርጫ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ነው፡፡