በሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ዛሬ እየተካሄደ ባለው ምርጫ ይበጀናል የሚሉትን አካል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን መራጮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ዛሬ እየተካሄደ ባለው ምርጫ ይበጀናል የሚሉትን አካል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን መራጮች ገለጹ
ጅግጅጋ/አሶሳ ፤ ሰኔ 16/2016 (ኢዜአ)፦ በሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው ምርጫ ይበጀናል የሚሉትን አካል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው መራጮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድጋሚ እና ቀሪ ምርጫ እንዲካሄድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በዛሬው እለት በሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ምርጫ እየተካሄደ ነው።
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በሚካሄደው የድጋሚ ምርጫ ኢዜአ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ መሀመድ አብዲ በሰጡት አስተያየት፤ በምርጫው ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የከተማውን ልማት ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ እጩዎችን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።
የምርጫ ሂደቱም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ ሆኖ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙርሰል መሀመድ ናቸው።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አብዲረሺድ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ በድምጽ አሰጣጡ የምርጫ ህጉን በጠበቀ መልኩ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በከተማው ቀበሌ 05 ነዋሪ የሆኑት አቶ ሚሬ መሀመድ በአካባቢያቸው የተዘጋጀውን የምርጫ ጣቢያ ዝግጅት ስራዎችን በቅርበት መመልከታቸውን ገልጸው፤ ለምርጫው መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚካሄደው የድጋሚና ቀሪ ምርጫ መራጮች የሚፈልጉትን አካል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በአሶሳ ከተማ በሚካሄደው የድጋሚ ምርጫ ላይ ለመምረጥ ከተገኙት መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ታከለ ኢዶሳ፤ በምርጫው ''የመምረጥ እድል በመጠቀም ለክልሉ ብሎም ለአገሪቷ የሚጠቅም እጩ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ'' ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አንበሳ ሰዲ በበኩላቸው ''የእኔ አንድ ድምጽ ዋጋ እንዳላት ስለምረዳ እና እንዳትባክን በመጠንቀቅ በጣቢያው በመገኘት የድምጽ መስጫ ካርድ አግኝቻለሁ'' ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን ክፍል ሠራተኛ እና የአሶሳ ሆሀ እና የአሶሳ መገሌ ምርጫ ክልሎች አስተባባሪ ወይዘሪት ሀያት መሃመድ በምርጫ ክልሎች ስር 102 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡