ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ልኬት በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መከናወኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ልኬት አሁን ያለበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መከናወኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ገለጹ፡፡

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ቅድመ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ከቀናት በፊት ተካሂዷል።  

በቅድመ ማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም በዛፍ መጨፍጨፍ ሳቢያ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 3 በመቶ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን አንስተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሰራው ስራ ግን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ  አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር  ከበደ ይማም፤ የኢትዮጵያ የደን ልማት ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመሆን አሁን ያለበት ሁኔታ መጠናቱን ተናግረዋል። 

በጥናቱ አለም አቀፍ የደን ምርምር ማዕከል፣ ሴንተር ፎር ትሮፒካል አግሪካልቸር፣ ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጅኦ ስፓሻል ኢንስቲቱት የተሳተፉ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የጥናቱ ሂደት የተካሄደው በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን መስፈርት መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል።

መስፈርቶቹ ዛፎች ያረፉበት መሬት ስፋት ከ500 ካሬ ሜትር የማያንስ፣ ቁመታቸው ከሁለት ሜትር የማያንስ እና ቅርንጫፎቻቸው የሚሸፍነው መሬት ከ10 በመቶ የማያንስ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። 

በመስፈርቶቹ መሰረት ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የደን ሽፋን ልኬት መስፈርት በተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡

በነዚህ መስፈርቶች መሰረት በተደረገ የደን ሽፋን ልኬት አሁን ላይ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

የደን ሽፋኑ ሲሰላ ዘመኑ የደረሰበት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትግበራ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰው ከፍተኛ የጂ-አይ-ኤስ እና የሪሞት ሴንሲንግ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ የሚተገበር ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያውያን ለትውልዱ ዕዳ ላለማውረስ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስገንዘባቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም