ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2016(ኢዜአ)፦ በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በዛሬው እለት ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች አልተሸነፈም። 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 5 ግቦችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ57 ነጥብ በሊጉ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ተቀምጧል። 

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 3 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በነዚህ 5 ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 5 ግቦች ተቆጥሮበታል።

በጊዜያዊው አሰልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ43 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ መቻል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 ከፍ ያደርጋል።

መቻል ትናንት ባደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡናን  4 ለ 1 በማሸነፍ ከንግድ ባንክ ጋር በነጥብ እኩል የሆነ ሲሆን በግብ ክፍያ ተበልጦ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። 

በ28ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሀምበሪቾ ከወላይታ ድቻ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ የሚመራው ሀምበሪቾ ባለፉት 5 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ተሸንፏል። 

በ5ቱ ጨዋታዎች ያስቆጠረው 1 ግብ ብቻ ሲሆን 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል።  ሀምበሪቾ በ8 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

ወላይታ ድቻ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 3 ጊዜ ሽንፈት ሲገጥመው 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

በነዚህ 5 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል። በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በ32 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሀምበሪቾ በዛሬው ጨዋታ ከተሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርድ የመጀመሪያው ክለብ ይሆናል።

በሊጉ እስከ አሁን 21 ሽንፈቶችን ያስተናገደው ሀምበሪቾ በውድድር ዓመቱ ያሸነፈው 1 ጨዋታ ብቻ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መቻል ሲዳማ ቡናን 4 ለ 1 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም