በሀገሪቱ ከሦስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆነዋል-የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ ከሦስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆነዋል-የግብርና ሚኒስቴር
አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፦ የግብርና ምርት ብክነትና ብክለትን ለመቀነስ በተደረጉ ጥረቶች ከሦስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ጥናት መሠረት በድህረ ምርት የአያያዝ ሂደት ኋላቀርነት ምክንያት ከአዝዕርት ሰብሎች ከ20 እስከ 30 በመቶ እንዲሁም ከአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ከ40 እስከ 50 በመቶ የምርት ብክነት ይከሰታል።
ይህም አርሶና አርብቶ አደሩ ከግብርና ልማቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ እያደረገ መሆኑን ይሄው ጥናት ያሳያል።
የግብርና ሚኒስቴር ይህን ችግር ለመፍታት የተሻሻሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማስፋፋት ላይ ይገኛል።
ሚኒስቴሩ አርሶ አደሩ ከግብርና ሥራው ተገቢውን ጥቅም አግኝቶ ከተረጂነት ወደምርታማነት በሚያሸጋግሩ ጉዳዮች ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ መክሯል።
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ የምርት ብክነትና ብክለት ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በእነዚህ ሥራዎችም በአገሪቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅትም ከዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት ጋር በመተባበር ዘመናዊ የብረት ጎተራ እና የተሻሻሉ የምርት ከረጢቶችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የምርት ብክነትና ብክለትን ሙሉ ለሙሉ ከማስቀረት ባለፈ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጫና እንደሚያስቀሩ አስረድተዋል።
እንደ ዶክተር መለስ ገለጻ የተሻሻሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ ምርታማነትን በማሳደግ በአገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል ለተያዘው ግብ መሳካት ፋይዳው የጎላ ነው።
ሚኒስቴሩ በቀጣይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በሀገሪቱ ያሉ አርሶ አደሮች የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ተጠቅመው የምግብ ሉዐላዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ በትኩረት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ምትኩ መላኩ በበኩላቸው፣የተሻሻሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች የምርት ብክነትና ብክለትን ከማስቀረት አኳያ ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ የአርሶ አደሩ ፍላጎት በየጊዜው እያደገ መጥቷል ብለዋል።
ለእዚህም በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የተሻሻለ የምርት ከረጢት እንዲሁም ከ4ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የብረት ጎተራ ተጠቃሚ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂዎችን ሁሉም አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"በክልሉ ዘመናዊ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል" ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት በክልሉ ጋርዱላ ዞን በርካታ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ከዘንድሮ የመኸር እርሻ ጀምሮ ይህን ተሞክሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋፋት ታቅዶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በመድረኩ የግብርና ሚኒስተር፣ የተለያዩ ክልሎች የግብርና ዘርፍ የሥራ ሃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ተሳትፈዋል።
ከመድረኩ በተጨማሪ በጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ የአርሶ አደሮችን የድህረ ምርት ቴክሎጂ አጠቃቀም ሂደት ተጎብኝቷል።