ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ጸጋዎች በማልማት ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ እንደምትችል ከለውጡ ወዲህ የታዩ ስኬቶች ማሳያዎች ናቸው - ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ጸጋዎች በማልማት ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ እንደምትችል ከለውጡ ወዲህ የታዩ ስኬቶች ማሳያዎች ናቸው - ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ጸጋዎች በማልማት ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ እንደምትችል ከለውጡ ወዲህ የታዩ ስኬቶች ማሳያ መሆናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ አገራዊ ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ ውይይት አካሂደዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ዘርፈ-ብዙ ጸጋዎች ያሏት አገር ናት ብለዋል።
እነኚህን ጸጋዎች በሚፈለገው መልኩ ባለማልማቷም ለዘመናት ከተረጂነት መውጣት እንዳልቻለች ጠቅሰው፤ ተረጂነት አንገት የሚያስደፋ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እንደ አገር ያሉንን እምቅ ኃብቶች በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው፤ ተረጂነትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እንደሚቻል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም የልማት ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ እንደሆኑም አንስተዋል።
ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ጠቅሰዋል።
ለውይይቱ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
መግባባት፣ መዘጋጀትና በተቀናጀ መንገድ የልማት ሥራን ማፋጠን ክብረ-ነክ የሆነውን ተረጂነትን ማስወገድ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮች እንደ ሀገር ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ይበል የሚያስብሉ ናቸው ብለዋል።
በበጋ የመስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎችም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ትልቅ ጉልበት የሚሆኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
እያንዳንዱ ሰው ተረጂነትን ለማስቀረት የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ኃብቶች በማልማት ከተረጂነት መላቀቅ እንደምትችል ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት አቅም አንጻር ተረጂ ሆና መቀጠል እንደሌለባት አንስተው፤ ብልጽግና ይዞ የተነሳቸውን ራዕዮች እውን ለማድረግም የተረጂነት አስተሳሰብን ማስወገድ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባሏት እምቅ የተፈጥሮና ሌሎች ኃብቶች የራሷን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደምትችል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ የተደረጉ ኢኒሼቲቮች ማሳያ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ከተረጂነት አስተሳሰብ ማላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ዘመኑ የሚፈልገው አርበኝነት ነው ብለዋል።
ከተረጂነት ለመውጣት የሥራ ባህልና የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚስፈልግ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ኢኒሼቲቮቹን ከግብ ማድረስ እንደሚገባም ገልፀዋል።
ሁሉም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በውይይቱ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ተግኝተዋል።