ለነዋሪዎች ምቹ፣ ውብና ለቀጣይ ትውልድ የሚሸጋገሩ ከተሞችን ለመገንባት ራዕይ ይዘን እየሰራን ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ለነዋሪዎች ምቹ፣ ውብና ለቀጣይ ትውልድ የሚሸጋገሩ ከተሞችን ለመገንባት ራዕይ ይዘን እየሰራን ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፡- ለነዋሪዎች ምቹ፣ ውብና ለቀጣይ ትውልድ የሚሸጋገሩ ከተሞችን ለመገንባት ራዕይ ይዘን እየሰራን ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የሸገር ከተማ ታላቁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ አስጀምረዋል።
የመንገዱ ግንባታ ሁሉንም የሸገር ከተማ ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝና በዓይነቱ ልዩ የሆነ መንገድ ሲሆን፤ ግንባታው ዛሬ በኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ተጀምሯል።
መንገዱ በአጠቃላይ 150 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚገነባ መሆኑ ተገልጿል።
በመጀመሪያ ምዕራፍ 38 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ወጪውም ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑም ተገልጿል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታው ኩራ ጂዳ፣ለገጣፎ ለገዳዲ፣ገላን እና ኮዬፈጬ ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝ ሲሆን በኦ ሲ ጂ በተሰኘ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ይገነባል ተብሏል።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ከተሞች ውብና ለነዋሪዎች ምቹና ዘመናዊ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ከተሞች ሲያድጉ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ይዘው እንዲዘምኑና ነዋሪዎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለየ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሸገር ከተማ "የዘመናዊ ከተማ ግንባታ" ሕዝቡ ከከተማዋ ጋር እንዲያድግ ከከተማዋ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጎ የሚገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለመንገዱ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የሥራ ባህልን ማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ተወዳዳሪና ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር ሕዝብ ከከተሞች ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን የበለጠ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ከተማዋን ስማርት ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከማሳደግ በተጨማሪ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቃሜታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።
ግንባታው የከተማዋን የአስፋልት መንገድ ሽፋኑን ወደ 413 ኪሎ ሜትር እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
በሸገር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ግንባታ መጀመሩ ከዚህ በፊት በመንገድ እጦት የነበረውን ችግር እንደሚፈታላቸውን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
መንገዱ በመሰራቱም በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለግንባታው መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር የክልሉና የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።