በሶማሌ ክልል ለሚካሄደው 6ተኛው ዙር የድጋሚ ምርጫ የሚያገለግል የምርጫ ቁሳቁስ ለየምርጫ ጣቢያዎች ተሰራጨ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ለሚካሄደው 6ተኛው ዙር የድጋሚ ምርጫ የሚያገለግል የምርጫ ቁሳቁስ ለየምርጫ ጣቢያዎች ተሰራጨ
ጅግጅጋ ፤ሰኔ 15 / 2016 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ ለሚካሄደው 6ተኛው ዙር የድጋሚ ምርጫ የሚያገለግል የምርጫ ቁሳቁስ ለየምርጫ ጣቢያዎች ተሰራጨ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን የስራ ክፍል አስተባባሪና በጅግጅጋ ከተማ በሚካሄደው 6ተኛው ዙር የማሟያ ምርጫ አስተባባሪ አቶ ሀይለየሱስ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በነገው እለት በጅግጅጋ ከተማ በምርጫ ክልል ሁለት የ6 ተኛው ዙር የድጋሚ ምርጫ ይካሄዳል።
በከተማው ለሚካሄደው የድጋሚ ምርጫ አንድ የምርጫ ከልል፣ አራት አስተባባሪዎችና 123 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ለምርጫ ጣቢያዎቹ 615 የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች መመልመላቸውን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሃይለየሱስ ወርቁ ገለጻ፤ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የምርጫ ቁሳቁስ ለ123ቱም የምርጫ ጣቢያዎች ተሰራጭቷል።
ምርጫው ድጋሚ ምርጫ እንደመሆኑና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወሰነው መሰረት የመራጮች ምዝገባና መረጣ በነገው ዕለት እንደሚሆን ነው ያመለከቱት።
በከተማው በሚካሄደው የድጋሚ ምርጫ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሶስት የግል እጩዎች እንደሚወዳደሩም አክለዋል።
ምርጫው ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ በየምርጫ ጣቢያው ከተመደቡት የምርጫ አስፈጻሚዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቋቋመ እና ችግሮች ሲከሰቱ ምላሽ የሚሰጥ አምስት የክትትል ቡድን መደራጀቱን ተናግረዋል።