ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና የሶስተኝነት ደረጃን በድጋሚ ተረክቧል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ 1 አሸንፏል። 

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አጥቂው አንተነህ ተፈራ በ33ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ እንዲሆን አስችሏል።

ይሁንና አጥቂው ያሬድ ዳርዛ በ47ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ መድንን አቻ ያደረገችውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የኢትዮጵያ መድን አምበል አብዱልከሪም መሐመድ በ68ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ ያስቆጠረው ግብ ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ50 ነጥብ ለአንድ ቀን አጥቶት የነበረውን 3ኛ ደረጃ በድጋሚ ከባህር ዳር ከተማ ተረክቧል።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ መድን በ37 ነጥብ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ መድን ከ10 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በኋላ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

በ28ኛ ሳምንት ሌላኛው መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም