ቀጥታ፡

የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ  

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ለምታከናውነው ተግባር የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ሙያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ። 

ኢትዮጵያ በፈጠራ ክህሎት የታነጸ አምራች የሰው ኃይል በማፍራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፍ የፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያዎችን በማድረግ እየተገበረች ትገኛለች። 

ከእነዚህ መካከል በተግባር የተደገፈ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በማፍለቅ አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ትልቅ ሚና ያላቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው።

የጂ አይ ዜድ የዘላቂ ትምህርትና ሥልጠና መርኃ-ግብር ኃላፊ ሞሃመድ አሊ ካን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት እያከናወነች ላለው ተግባር በትብብር እየተሰራ ነው።

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በፈጠራና ክህሎት ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ተግባራዊ እየተደረገ ላለው ፖሊሲ የቴክኒክና የሥልጠና ዘርፍ የሙያ ድጋፍ በማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን ላይ ደግሞ በዘርፉ ተቋማት ዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እያገዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ድጋፍ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።

 በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የትምህርትና የሥልጠና ዘርፉን በደንብ አሰናስሎ ከማስኬድ አኳያ የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላና ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ በሙያ የተቃኘ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል።

ፖሊሲው ከሙያ ሥልጠና አኳያ ከአስተሳሰብ ጀምሮ ያሉ ዝንፈቶችን የሚያስተካክልና የሥልጠና ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን የሚያስተናግድ ሥርዓት የሚዘረጋ መሆኑም ተጠቁሟል።

ኃላፊውም ይህንን በመደገፍ፤ አዲሱ ፖሊሲ ለቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ፣ ለጥራት እንዲሁም ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፖሊሲው በአግባቡ ከተተገበረ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሥርዓትን በማሻሻል በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል።

የግሉ ዘርፍ ከሥልጠና ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት በተግባር የተደገፈ ክህሎትና እውቀት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብት የሚያሳልጡ በፈጠራ ክህሎት የታነጹ ሙያተኞችን ለማፍራት መንግሥት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማሳካት በትብብር መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉም ኃላፊው አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም