ቀጥታ፡

መንግሥት የገቢ አሰባሰብ አቅሙን ማጠናከርና ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት አለበት - የምጣኔ ኃብት ምሁራን

አዲስ አበባ፤ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፦መንግሥት የገቢ አሰባሰብ አቅሙን በማጠናከርና በማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ኃብት ምሁራን ገለጹ።  

የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሆኖ ሰኔ 4 ቀን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወቃል።       

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በማብራሪያቸው ረቂቅ በጀቱ ከሁለተኛው አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተጣጣመ መልኩ መዘጋጀቱንና ጤናማ የፊስካል ሥርዓት ማረጋገጥን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚሁ መሠረት የ2017 ዓ.ም ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሆኖ መቅረቡን ይህም ከተያዘው በጀት ዓመት አንጻር የ21 ነጥብ 1 በመቶ ወይም የ169 ነጥብ 56 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው መግለጻቸው የሚታወስ ነው።  

ከዚህም ውስጥ 451 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመደበኛ፣ 283 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጪዎች እና 236 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ የተመደበ ነው።

ለክልል መንግሥታት ከተመደበው የበጀት ድጋፍ 14 ቢሊየን ብር የሚሆነው ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እንደሚውልም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።  

ከተያዘው በጀት ውስጥ 502 ቢሊየን ብር ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ መታቀዱንና በአጠቃላይ 563 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለማሰባሰብ መታሰቡን ጠቁመዋል።

ከተመደበው በጀት 139 ነጥብ 3 ቢሊየን ብሩ ለዕዳ ክፍያ እንደሚውልም ገልፀዋል። 

ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት፤ የ2017 በጀት 1 ትሪሊየን ብር የሚጠጋ ሆኖ በረቂቅ በጀት መዘጋጀቱ፤ የአገሪቱ በጀት በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል።  

እንዲያም ሆኖ መንግሥት የገቢ አሰባሰብ አቅሙን ማጠናከርና ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት አለበት ነው ያሉት። 

የኢኮኖሚ ባለሙያ ደረጀ ደጀኔ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ መንግሥት የአገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ የገቢ የማሰባሰብ ሥልቱን ማዘመንና ማጠናከር አለበት ብለዋል።

የታክስ መሠረቱን ማስፋትና አቅምን ማሳደግ ላይ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ የገለጹት ባለሙያው፤ ግልጽ የሆነ አሠራር መከተል በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ስኬታማ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጠቃሚ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል።   

ሙስናና ብልሹ አሠራር የሚሰበሰበው ገቢ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል የማድረግ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ከብልሹ አሠራር የፀዳ አካሄድ መከተል እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።   

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ማክሮ ኢኮኖሚስት ተወልደ ግርማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት የገቢ መሰብሰብ አቅሙን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።  

ታክስ ለአንድ አገር እድገት ወሳኝ ቢሆንም ፍትሃዊ እንዲሆን ማድረግ ይገባል ያሉት ባለሙያው፤ ታክስ ፍትሃዊ ካልሆነ የዜጎች የመክፈል ፍላጎትና ተነሳሽነት ላይ አሉታዊ ጫና ሊያሳድር ይችላል ብለዋል። 

ባለሙያዎቹ፤ መንግሥት በዋናነት ግብርናውን በመደገፍና ኢንዱስትሪውን በማስፋፋት ላይ ትኩረት በማድረግ የአገሪቱን እድገት ለማስቀጠል መሥራት እንዳለበትም ጠቅሰዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም