የሲቪል ማኅበራት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማኅበራት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016(ኢዜአ)፦ የሲቪል ማኅበራት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ጠየቁ።
ጽህፈት ቤቱ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን የሲቪል ማኅበራት ያላቸውን ሚና በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል።
የምክክር መድረኩ "የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ" በሚል መሪ ኃሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ግድቡ ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
በመሆኑም ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ከኅብረተሰቡ ጎን ለጎን የሲቪል ማኅበራትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያያዥ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፅሁፎች ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።