ተረጂነትን የማስቀረት ሀገራዊ ግብን ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት - አለሙ ስሜ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ተረጂነትን የማስቀረት ሀገራዊ ግብን ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት - አለሙ ስሜ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በማልማት ተረጂነትን ለማስቀረት የጀመረችውን ግብ ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶር) ገለጹ።
የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት እያካሄዱ ነው።
ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ጸጋዎች ያሏት ሀገር ናት ብለዋል።
እነኚህን ጸጋዎች በሚፈለገው መልኩ ባለማልማቷም ለዘመናት ከተረጂነት መውጣት እንዳልቻለች ተናግረዋል።
ተረጂነት አንገት የሚያስደፋ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እንደ ሀገር ያሉንን እምቅ ሃብቶች በአግባቡ መጠቀም ይገባናል ብለዋል።
ተረጂነትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እንደሚቻል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም የልማት ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ እንደሆኑም አንስተዋል።
ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ጠቅሰዋል።
የሀገር ሉዓላዊነት ምልዑ የሚሆነው የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ እና ምርታማነትን በእጅጉ በማሳደግ ራስን የመቻል ግብ ሲረጋገጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አኳያ አመራሩ ትልቅ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።
የዛሬው ውይይት ዋና ዓላማ አመራሩ ከተረጂነት ለመላቀቅና ምርታማነትን ለማሳደግ የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ መግባባት ለመፍጠር መሆኑንም ገልጸዋል።
ለውይይቱ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፤ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
መግባባት፣ መዘጋጀት እና በተቀናጀ መንገድ የልማት ስራን ማፋጠን ክብረ ነክ የሆነውን ተረጂነትን ማስወገድ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
በውይይቱ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተግኝተዋል።