በጋምቤላ ክልል በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ጋምቤላ ፤ሰኔ 15/2016 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ከ12 ሺህ 850 በላይ ተማሪዎች ለፈተናው እንደሚቀመጡም ተገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የፈተና ውጤት ታሳቢ በማድረግ ለዘንድሮው አገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ ለመሆን ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።
በፈተናው ያለፉት ዓመታት ውጤት እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር ዝቅተኛ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ ይህን ታሳቢ በማድረግ ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት ለማብቃት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተለይም የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በማጠናከር በዋና ዋና የትምህርት ዓይነቶች ከመደበኛ የትምህርት ሰዓት በተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱንም አስታውቀዋል።
የፈተናውን ሂደትም ስኬታማ ለማድረግ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የተለያዩ ተቋማት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አቶ ላክደር ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በበይነ መረብ የሚሰጠውን ፈተና እንዲወሰዱ ለተመረጡ ተማሪዎች የኮምፒዩተር ክህሎታቸውን የማሳደግና የማለማመድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት 12 ሺህ 857 ተማሪዎችን በጋምቤላና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚያስፈትንም ኃላፊው አስረድተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የታየውን የውጤት ማሽቆልቆል ለመቀልበስ በትምህርት ዘመኑ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ በጋምቤላ ከተማ የኢለይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዋሲሁን ደጀኔ ናቸው።
ትምህርት ቤታቸው ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ በትርፍ ሰዓት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን ለፈተናው ሲያዘጋጅ ቆይቷል ብለዋል።
የጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ጋልዋክ ፓታል በመጀመሪያውና በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት የተሰጠውን ትምህርት በአግባቡ በመከታተልና በማንበብ ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።
በኢለይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪው ወንድወሰን አለባቸው በሰጠው አስተያየት በመጪው ወር ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
በትምህርት ዘመኑ በመደበኛና በትርፍ ሰዓት በትምህርት ቤቱና በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ለፈተናው የሚያበቃውን ትምህርት በበቂ ሁኔታ መከታተሉንም ተናግሯል።