የሸገር ከተማ ታላቁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ ታላቁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2016(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሸገር ከተማ ታላቁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አስጀመሩ።
በግንባታው ማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፣ አባ ገዳዎችና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የመንገዱ ግንባታ በሸገር ከተማ የሚገኙ ሁሉንም ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝና በዓይነቱ ልዩ የሆነ መንገድ መሆኑ ተገልጿል።
የዚህም የመንገድ ፕሮጀክት ዛሬ በኩራጂዳ ክፍለ ከተማ ተጀምሯል።
መንገዱ በአጠቃላይ 150 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚገነባ መሆኑም ተጠቁሟል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 38 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ግንባታ ይከናወናል ተብሏል።
ይህም ኩራጂዳ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ገላንና ኮዬፈጬ ክፍለ ከተሞችን የሚያገናኝ ነው ተብሏል።