በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚያነቃቁና የሚያበረታቱ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረጉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚያነቃቁና የሚያበረታቱ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረጉ ተጠየቀ
ቦንጋ፤ ሰኔ 14/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚያነቃቁና የሚያበረታቱ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረጉላቸው በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ጠየቁ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ የፋይናንስ፣ የቦታ እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና የአምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን እና ባዛር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተሳተፉ ኢንተርፕራይዞችም የመስሪያና የመሸጫ ቦታን ጨምሮ የአምራች እንዱስትሪውን ዘርፍ የሚያነቃቁና የሚያበረታቱ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ከኢንተርፕራይዞች መካከል የሀይማኖት እንጨትና ብረታብረት ማምረቻ ማህበር ዋና ሰብሳቢ ወጣት ተሾመ ካሳው እንደገለጸው፣ ማህበሩ ከሁለት ዓመት በፊት ሥራውን በሦስት ሰው መጀመሩንና በአሁኑ ወቅት ለ9 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
የመስሪያ ቦታ ባለመመቻቸቱ ለቤት ኪራይ በዓመት እስከ 60 ሺህ ብር ድረስ እንደሚያወጡ ገልጸው፣ ማህበሩ የራሱ መስሪያ ቦታ አለመኖር ገንዘብ ለመበደር እንቅፋት እንደሆነበት ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ሃይልና ለስራቸው የሚያግዙ የተለያዩ ማሽኖች አለመኖር ስራቸውን ለማሳደግ እንቅፋት እንደሆነባቸው የገለጸው ወጣት ተሾመ፣ የሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የዳማሲል መዓዛማ ዘይቶችና ውጤቶች፣ የቅመማቅመም ማቀነባበሪያ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ራሔል ህሩይ በበኩላቸው፣ በአርሶ አደሩ የግብርና ምርት ላይ እሴት ጨምረው በማምረት ለፋብሪካዎች እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል።
በቀጣይ ማህበሩ ከግብርና ምርቶች የተለያዩ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን የማምረት እቅድ እንዳለው ጠቁመው፣ ለዕቅዱ መሳካት መንግስት የገንዘብ ችግራቸውን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የአምራች ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ምርታቸውን ለእይታ እንዲያቀርቡ መደረጉ ምርታቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቀጣይ ሥራቸው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ( ዶ/ር )ዘርፉን ለማነቃቃት በመንግስት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በተለይ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ማነቆ የሆኑ የፋይናንስ፣ የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታዎች እንዲሁም መሠረተልማት የማሟላት ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።
በገበያው ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን ምርትን በተሻለ ጥራት ማምረት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የመንግስት መዋቅሮች የኢንተርፕራይዞችን ምርት በመግዛት አምራቾችን ማበረታታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በክልሉ በጥራትና በብዛት የሚሰሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በየደረጃው ባሉ ባለድርሻ አካላት ተገቢ ድጋፍ እንዲያገኙ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ሲሉም ኢንጂነር ነጋሽ ( ዶ/ር )ገልጸዋል።
የክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት ምጣኔ 48 በመቶ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ ናቸው።
መድረኩ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ሃይል ችግር እንዲፈታ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልል ደረጃ የተዘጋጀው የገበያ ማበረታቻ አዋጅም አምራቾች በገበያ ትስስር የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አምራች ኢንተርፕራይዞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።