ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት የሕክምና ተቋማትን አጠቃላይ አገልግሎት እውቅና መስጠት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት የሕክምና ተቋማትን አጠቃላይ አገልግሎት እውቅና መስጠት (አክሪዴት ማድረግ) በቅርቡ ሊጀምር መሆኑን ገለጸ። 

አገልግሎቱ የዓለም የአክሪዲቴሽን ቀንን በተለያዩ መርኃ ግብሮች አክብሯል፤ አክሪዲቴሽን አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። 


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ መተማመንን ለማሳደግ፣ የሕዝብ ደህንነትና የአኗኗር ደረጃን ለማሻሻል እንዲሁም የኅብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ የጥራትና አክሪዲቴሽን መሰረተ ልማት ግንባታ ወሳኝ ነው።

መንግሥት ለጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ለመጠናከር ከአጋር አካለት ጋር በመተባበር ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት፣ የደረጃዎች ኢኒስቲትዩት፣ የሥነ-ልክና የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን ቢሮችና ዘመናዊ የላቦራቶሪዎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አክሪዴቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ በበኩላቸው፤ የጤና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ አገልግሎቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የጤና ተቋማትን እውቅና ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ ነው።


 

እውቅና አገልግሎቱን ለመጀመር ደረጃዎች /ስታንዳርድ/፣ መመሪያ እንዲሁም የማበረታቻ አሰራርን ለመዘርጋት የሚከናወኑ ተግባራት እየተጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ የተወሰኑ ሆስፒታሎችን እውቅና መስጠት እንጀምራለን ሲሉም ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ ቦንሳ ገለጻ፤ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የሚፈትሹ ተቋማት፣ የተስማሚነትና ምዘና ተቋማት፣ የላብራቶሪ ሕክምና ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ እስካሁን ከ80 በላይ ለሚሆኑ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በስድስት ወሰኖች የዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ፎረምና የዓለም አቀፍ ላቦራቶሪ ኦሶሴሽን ኮኦፕሬሽን አባል መሆኑን ገልጸዋል።

በአገልግሎቱ እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ መሸጥ የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ዛሬ በተካሄደው የዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ቀን አከባበር ላይ በተለያዩ መስኮች መስፈርቱን ላሟሉ ተቋማት የአክሪዲቴሽን /እውቅና / አሰጣጥ መርኃ ግብር ተካሂዷል።

እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቤል አንበርብር ለኢዜአ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በግብርና ምርቶች፣ መጋዘንና ላቦራቶሪ ኢኒስፔክሽን ዓለም አቀፍ እውቅናን አግኝቷል።


 

እውቅናው ድርጅቱ ኢኒስፔክሽን /ቁጥጥር/ የሚያደርጋቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት።

የውዳሴ ሜዲካል አድቫንስድ ላቦራቶሪ ሥራ አስኪያጅ ሚዛን ገብረዮሃንስ በበኩላቸው እውቅናው ለታካሚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በምናደርገው ጥረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርልናል ብለዋል።


 

 የዓለም የአክሪዲቴሽን ቀን በኢትዮጵያ ለ14 ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ነው የተከበረው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም