ሚኒስቴሩ የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀና እያስፋፋ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀና እያስፋፋ መሆኑን ገለጸ
ጊዶሌ ፤ ሰኔ 14/2016 (ኢዜአ)፦ የግብርና ምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀና እያስፋፋ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) የተመራና የፌዴራል እና የክልል የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋርዱላ ዞን የድህረ ምርት ብክነት ቅነሳ ቴክኖሎጂዎችን ጎብኝቷል።
ቡድኑ በዞኑ ደራሸ ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች አርሶ አደሩ የሚጠቀበትን "ፖሎታ" የተሰኘውን ባህላዊ የመሬት ውስጥ ጎተራ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ሚኒስቴሩ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሩ ያቀረባቸው ዘመናዊ የብረት ጎተራዎች እና የተሻሻሉ የምርት ማስቀመጫ ከረጢቶችም በቡድኑ አባላት ተጎብኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው መለስ መኮንን(ዶ/ር) በእዚህ ወቅት እንደገለጹት የድህረ ምርት ብክነት በአገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
ሚኒስቴሩ የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ መለሰ መኮንን(ዶ/ር) ገለጻ ጉብኝቱ የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ በሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ ነው።
አርሶ አደሩ ከባህላዊ ጎተራ ተላቆ ዘመናዊ ጎተራን መጠቀሙ የምርት ብክነትን ከመቀነስ ባለፈ እንደ ሀገር የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በመስክ ምልከታውም በጋርዱላ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘመናዊ ጎተራዎችን መጠቀም መጀመራቸውን እንዳረጋገጡም ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከሚኒስቴሩ በተጨማሪ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የሲዳማ ክልሎች የዘርፉ ሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።