ቀጥታ፡

በቀጣይ አስር ቀናት የክረምት ዝናብ በሚያገኙ የአገሪቷ አካባቢዎች የዝናብ ሥርጭትና መጠን ይጨምራል  

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2016(ኢዜአ)፦ በቀጣይ አስር ቀናት የክረምት ዝናብ በሚያገኙ የአገሪቷ አካባቢዎች የዝናብ ሥርጭትና መጠን እንደሚጨምር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ገለጸ። 

በአንዳንድ አካባቢዎች ሊፈጠር የሚችል ከፍተኛ እርጥበትና ጎርፍ  በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

ኢንስትቲዩቱ ይህን ያለው ከዛሬ ሰኔ 14 ጀምሮ ለቀጣይ አስር ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አዝማሚያ አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ነው።

በቀጣይ አስር ቀናት በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ መካከለኛው፣ ምስራቅና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያን አካባቢዎች የዝናብ ሥርጭትና መጠን ይጨምራል ብሏል ኢንስቲትዩቱ።

በዚህም በኢሊባቦር፣ በወለጋ፣ በሀረርጌ፣ በአርሲ፣ በሸዋ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በጎጃም፣ በትግራይ ክልል፣ በቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች በሚገኙ አብዛኛው ዞኖች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ሲዳማና ሀረርክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ አስተዳደር አብዛኛው ዞኖች ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ እንደሚያኙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በምሥራቅ ሀረርጌ፣ ምስሥራቅና ምዕራብ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ኤረር፣ ጀረር፣ ኖጎብ፣ አፍዴር፣ ሊበንና ደዋ፣ ቅብልቲ፣ ፈንቲ፣ አውሲ፣ ሀሪ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በጋምቤላ ኑዌርና ኢታንግ ዞኖች ደግሞ ቀላል ዝናብ ይዘንባል።

በቀጣይ አስር ቀናት በአባይ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ-ጊቤ፣ ደናክሌ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ላይኛው ዋቢ ሸበሌና ገናሌ ተፋሰሶች ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚኖራቸውም ትንበያው ያሳያል።

በትንበያው መሰረትም በተጠቀሱ ቀናት የሚኖረው ዝናብ መጠንና እርጥበት ለእርሻ ሥራና ለአርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሳርና የውሃ አቅርቦት ለማጎልበት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የሚፈጠረው ከፍተኛ እርጥበትና ጎርፍ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም