በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።
አዳማ ከተማ ከባህርዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል፤1 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በነዚህ 5 ጨዋታዎች 9 ግቦችን ሲያስቆጥር 6 ጎሎችን አስተናግዷል። አዳማ ከተማ በ44 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባህርዳር ከተማ ባለፉት 5 የሊግ በጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎች ተቆጥረውበታል። በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህርዳር ከተማ በ46 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። 1 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ድሬዳዋ በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 7 ግቦችን አስተናግዷል።
በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በ40 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። 3 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ግቦች ተቆጥረውበታል። በግርማ ታደሰ የሚሰለጥነው ሀድያ ሆሳዕና በ35 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ሻሸመኔ ከተማን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ሃዋሳ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።