ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃና ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ለግብርና ምርታማነት ጉልህ ፋይዳ አለው-ዓለም አቀፉ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃና ለመሬት አስተዳደር የሰጠችው ትኩረት ለግብርና ምርታማነትና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ፋይዳ እንዳለው ዓለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የዓለም አቀፍ የውሃ አሰተዳደር ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ በግብርና መስክ ያስመዘገበችውን የልማት ውጤትና ቀጣይ ተግባራትን  ማገዝ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሂዷል።

በአውደ ጥናቱም በኢትዮጵያ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሬት አስተዳደር፣ ውሃ እና የአካባቢ ጥበቃ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በተቀናጀ መልኩ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመሬት፣ በውሃ፣ በደን ልማት የጀመረችው ስራ ለአየር ጠባይ ምቹ የግብርና ስርዓትን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።

የዓለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ አማረ ኃይለስላሴ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ ስንዴ እና ሌሎች የግብርና መስኮች ያስመዘገበችውን ስኬት በማሳያነት በመጥቀስ።

ኢንስቲትዩቱም ለአየር ጠባይ ተስማሚ የሆኑ የግብርና ስራዎችን ማስቀጠል ሚያስችል የፖሊሲ ግብዓትና በመሬት አስተዳደር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የጥናትና ምርምር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በትኩረት እሰራች ነው ብለዋል።
 


 

መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ከሚያደርገው ስኬታማ ልማት በተጓዳኝ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የተራቆተ መሬት እንዲያገግም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋርም አፍሪካም ባለፉት ዓመታት 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት እንዲፈጠር ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን አስረድተዋል።

በአውደ ጥናቱ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ ጥናትና ምርምርን መሰረት በማድረግ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እንደሚሰሩ አንስተዋል።

የፋርም አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሸዊት አማኔኤል፥ ፋርም አፍሪካ ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥብቃን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አርሶ አደሩ በበጋና በክረምት እንዲያለማ የግብዓት አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ በማድረግ በቅንጅትና በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንሚቀጥል ገልፀዋል።

በአውደ ጥናቱ የዓለም አቀፉ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት፣ የፋርም አፍሪካ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም