የመቻል ስፖርት ክለብን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የመቻል ስፖርት ክለብን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016 (ኢዜአ)፦ ሕዝባዊ መሠረት ያለውን የመቻል ስፖርት ክለብን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥነ-ልቦና ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስቴር የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሥነ-ልቦና ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን፤ የመቻል ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ትልቅ አሻራ ያለው መሆኑን አንስተዋል።
የመቻል የስፖርት ክለብ ከሠራዊቱ ጋር የተሳሰረና ጠንካራ ሕዝባዊ ቁርኝት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ክለቡን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሰይፉ ጌታሁን(ዶ/ር)፤ ከሰባት ወር በፊት በንግዱ ዘርፍ ያሉ ባለኃብቶችና ከሌሎች ዘርፎች የተውጣጡ ግለሰቦች የተቋቋመው ቦርድ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ክለቡ የራሱ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በማድረግ በዘላቂነት እንዲደግፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን ለመፈራረም እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክለብ የስፖርት አስተዳደር ሥርዓት ሳይንሳዊ አሠራርን የተከተለ እንዲሆን አደረጃጀቱን የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የራሱን ስታዲየም መገንባትን ጨምሮ የስፖርት መሠረተ-ልማቶችን የማሟላት ተግባር በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራበትም ጠቅሰዋል።
የመቻል መጠናከር ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ የሚተርፍ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለታሪካዊው ክለብ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ በላይ ደጀን፤ የመቻል ስፖርት ክለብ ከምስረታው አንስቶ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስፖርት እድገት የማይተካ ሚና ያለውና አሁንም አስተዋጽዖ እንደቀጠለ አመልክተዋል።
ክለቡ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረጉ በርካታ ስመ-ጥር ስፖርተኞችን በማፍራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር የነበረው መቻል በዘንድሮው የሊግ ውድድር የዋንጫ ፉክክር እያደረገ ያለና ለኢትዮጵያ ታላቅ አሻራ ያሳረፈ ሕዝባዊ ክለብ መሆኑን አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመቻል ስፖርት ክለብን ሕዝባዊነት ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብን በአትሌቲክስ ስፖርት በመወከል የኢትዮጵያን ስም ያስጠሩት አንጋፋ አትሌቶች ሻምበል ቶሎሳ ቆቱና ሻምበል እሸቱ ቱራ የታሪካዊውን የስፖርት ክለብ ክብርና ዝና ዳግም ለመመለስ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች መደሰታቸውን ገልፀዋል።
መቻል በሚታወቅበት ስመ-ጥር አትሌቶችን የማፍራት ተግባር ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበትና ለዚህም የአትሌቲክስ ሙያተኞችን ማፍራት እንደሚገባው ተናግረዋል።
በመቻል ስፖርት ክለብ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ያሳለፉት መቶ አለቃ በኃብቱ ገብረማርያም፤ ክለቡ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና ቦክስን ጨምሮ ክለቡ በሚታወቅባቸው ስፖርቶች ተወዳዳሪነቱን ለመመለስ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የመቻል ስፖርት ክለብ የቀድሞ ታዋቂ ስፖርተኞች፣ የክለቡ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘንድሮ 80ኛ ዓመት የደፈነው መቻል ስፖርት ክለብ፤ የምስረታ በዓሉን የሚዘክርና የወደፊቱን የክለቡን ጉዞ መሠረት የሚያጸና "መቻል ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ መርሃ-ግብር ማዘጋጀቱ ይታወቃል።