ቀጥታ፡

ለማህበረሰቡ የተሻለ የመኖሪያ ካባቢን ለመፍጠር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠናከር ይገባል - አቶ ደስታ ሌዳሞ 

ሀዋሳ፤ሰኔ 13/2016 (ኢዜአ)፦ በክልሉ ለማህበረሰቡ የተሻለ የመኖሪያ ካባቢን ለመፍጠር የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ። 

በ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እንደሚከናወኑም ተጠቁሟል። 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ለኩ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት በማከናወን የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በይፋ አስጀምረዋል። 

አቶ ደስታ በዚሁ ወቅት በችግር ውስጥ ያሉትንና አቅመ ደካሞችን መርዳትና በቀጣይነት ማገዝ ተገቢ እንደሆነ ገልፀዋል። 

ተቀራራቢ የኑሮ ደረጃ ያለበትና የተሻለ የመኖሪያ ከባቢን ለመፍጠር ያለንን ለሌላቸው ማካፈልና የበጎነት ተግባርን ማጠናከር  ይገባናል ነው ያሉት። 


 

በዘንድሮ ክረምት በክልሉ ሁለት ሺህ የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ቤቶችን የማደስና በአዲስ መልክ መገንባትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራት ለማከናወን ግብ መያዙንም ጠቅሰዋል። 

በዚህ ረገድ በጎ ፈቃደኞች በጉልበት፣ በገንዘብና፣ በማስተባበር ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ባሻገር ባለሀብቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል። 

በዚህ ተግባር የሚሳተፉ በርካታ አቅም ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰው የአቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስና ከመገንባት በዘለለ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ማድረግ እንደሚያስፈልግልም አመልክተዋል። 

የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትና በተደራሽነት እየሰፋ መምጣቱን ገልፀዋል። 


 

በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ በጎ አመለካከትን በመፍጠርና በማነሳሳት ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የወጣቶችም ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል። 

በአሁኑ ክረምትም በአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ በደም ልገሳ፣ በማዕድ ማጋራት፣ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በ13 በተለዩ መስኮች አገልግሎቱ በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች እንደሚሰጥም ገልጸዋል። 

በዚህም ከ1 ሚሊዮን 689 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀው፤ ከመኖሪያ ቤት ግንባታና ዕድሳት አንጻር 1 ሺህ 200 ዕድሳትና 800 ቤቶች ደግሞ በአዲስ መልክ ይገነባሉ ነው ያሉት። 

ቤት ገንብቶ ቁሳቁስ ማሟላት ብቻ በቂ ባለመሆኑ አቅመ ደካሞችን በዘላቂነት ማቋቋም እንዲቻል መሬት ያላቸውን በእርሻ ሥራ የማገዝና መነገድ ለሚችሉ ደግሞ የመንቀሳቀሻ ገንዘብ የመስጠት ሥራም ይከናወናል ብለዋል። 

ዛሬ የቤት እድሳት ከተጀመረላቸው የለኩ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አማረች ኪንቻሞ ቤታቸው የፈራረሰና ዝናብ የሚያስገባ በመሆኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

ዛሬ ላይ የቤታቸው እድሳት በመጀመሩ እጅግ መደሰታቸውን ገልፀው እገዛ ያደረጉላቸውን አካላትም አመስግነዋል። 

"በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ"  በሚል መርህ በተጀመረው ክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎችና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም