ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር መካከል የተደረገውን 275 ሚሊዮን ዶላር የብድር ሥምምነት አዋጅ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር መካከል የተደረገውን 275 ሚሊዮን ዶላር የብድር ሥምምነት አዋጅ አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016 (ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር መካከል የተደረገውን 275 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር ሥምምነት አዋጅ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 33ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል ለሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገው የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጅን ማጽደቅ አንዱ ጉዳይ ነው።
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ብድሩ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር መካከል የተፈረመ ሲሆን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ 275 ሚሊዮን ዶላር ብድር የምታገኝ ሲሆን ብድሩ ከወለድ ነጻ መሆኑን አብራርተው፥ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የውኃ አቅርቦትና ማሻሻል፣የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ አቅርቦቶችን ማሳደግ፣ በአዲስ አበባና በተመረጡ ከተሞች የመጠጥ ውኃ እና ሳኒቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማዘመን ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በብድር ሥምምነቱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አድቆታል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ የአዋጁን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፥ አሁን ያለው የአረንጓዴ ልማት ሥራውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በፋይናንስ እንዲደግፍ ማድረግ ነው።
የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ረቂቅ አዋጁ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በሕግ ማዕቀፍ ለማስደገፍ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ የአረንጓዴ ልማት ሥራው ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል በሰፊው ሊሰራበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመሆኑም በአረንጓዴ ልማት የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ጉዳይ በረቂቅ አዋጁ ሊካተት ይገባል ሲሉም ነው የጠቆሙት።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል አቶ መስፍን እርካቤ በበኩላቸው የሚተከሉ ችግኞች በአግባቡ ክትትል እየተደረገባቸው እንዲጸድቁና ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የፌደራል የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅን የመረመረ ሲሆን በሦስት ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና የአካባቢና ማኀበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።