ማህበረሰቡ ስለ እንጉዳይ አመራረት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የእንጉዳይን ምርታማነት ለማሳደግ ከምርምር ስራዎች ጎን ለጎን ማህበረሰቡ ስለ አመራረት ሂደቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 3ኛውን ብሔራዊ የእንጉዳይ ቀን "እንጉዳይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለስራ እድል ፈጠራ" በሚል መሪ ሀሳብ አክብሯል።

በኢንስቲትዩቱ የባዮ-ቴክኖሎጂ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ግርማ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  በተጀመረው የልማት ስራ ለእንጉዳይ ምርታማነት ትኩረት ቢሰጥም በታሰበው ልክ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የእንጉዳይ ምርትና ምርታማነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ምርምር እያካሄደ ሲሆን በእንጉዳይ ልማት ለሚሰማሩ ወጣቶችም ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል።

ብሄራዊ የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ለታ ቱሉ  ማዕከሉ ስለእንጉዳይ አመራረት ክህሎት መር የግንዛቤ ስራዎችን እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።


 

ማምረት ለሚፈልጉ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች የእንጉዳይ ዘር ተደራሽ የማድረግና የድጋፍና ክትትል ስራን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።


 

በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ውጤቶች ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ሻሾ መገርሳ የእንጉዳይ ምርት ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር እንደ ሀገር ሰፊ ስራ ይጠበቃል ብለዋል።

  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም