11 አገራት ያዘጋጁት ታሪካዊው የአውሮፓ ዋንጫ 

አገራት ዓለም ዋንጫ፣ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችና ሌሎች ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ውድድሮች በጣምራ የማዘጋጀት ባህል ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ እየተለመደ መጥቷል። 

በተለይም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ይህ አዝማሚያ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የስፖርት ሁነቶችን በጋራ የማዘጋጀት ሀሳብ የሚመነጫው አንድ አገር ግዙፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ሲያስተናግድ ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የሚዳርግና አላስፈላጊ ጫና ውስጥ የሚከት በመሆኑ ነው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

ስፖርታዊ ሁነት በትብብር ማዘጋጀት አገራት ኢኮኖሚን ጨምሮ ሌሎች ጥቅሞችንና የሚኖሩ ጉዳቶችን እንዲጋሩ በማድረግ የስፖርት ውድድር አስተዳደርን ውጤታማ እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

የዓለም የእግር ኳስ ቤተሰብ ቀልብ ከሳቡ ስፖርታዊ ውድድሮች አንዱ በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ነው።

ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የአውሮፓ ዋንጫ የተጀመረው እ.አ.አ በ1960 ሲሆን የውድድሩ አዘጋጅ አገር የነበረችው ፈረንሳይ ነበረች።

እንግሊዝ እ.አ.አ በ1996 እስካሰናዳችው 10ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ድረስ ውድድሩ ሲካሄድ የቆየው በአንድ አገር አዘጋጅነት ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ አገር በላይ ውድድሩን ያዘጋጀው እ.አ.አ በ2000 በተካሄደው 11ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ነው።

ውድድሩን ያዘጋጁት አገራት ደግሞ ቤልጂየምና ኔዘርላንድስ ናቸው። በጣምራ የተካሄደውን ታሪካዊ ሁነት ፈረንሳይ ጣልያንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

እ.አ.አ በ2008 ኦስትሪያና ስዊዘርላንድ 13ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም ፖላንድና ዩክሬን እ.አ.አ በ2012 የተካሄደውን 14ኛ የአውሮፓ ዋንጫ በጋራ አዘጋጅተዋል።

ይሁንና እ.አ.አ በ2020 የተካሄደው 16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ከሁሉም የተለየና በጣም ያልተለመደ ነበር።

በወቅቱ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት የነበሩት ሚሼል ፕላቲኒ የአውሮፓ ዋንጫ የተጀመረበትን 60ኛ ዓመት ለማክበር ውድድሩ በተለያዩ አገራት እንደሚካሄድ ይፋ አደረጉ።

ፕላቲኒ ውድድሩን "የማይደገም የአንድ ጊዜ የአውሮፓውያውን የፍቅርና ወዳጅነት ሁነት" ሲሉም ገልጸውታል።

16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የተካሄደው በ11 የአውሮፓ አገራት በሚገኙ 11 ከተሞች ነው።

አዘርባጃን፣ ዴንማርክ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ሀንጋሪ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ሮማኒያ፣ ሩሲያ፣ ስኮትላንድና ስፔን ታሪካዊውን ውድድር በጋራ ያዘጋጁ አገራት ናቸው።

ውድድሩ ከእ.አ.አ ሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 12 2020 ይካሄዳል ተብሎ ቀን ቢቆረጥለትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 2021 ተዘዋውሯል።

ውድድሩን 13 አገራት እንደሚያዘጋጁት ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ቤልጂየም ውድድሩን ለማስተናገድ ስትገነባው የነበረው ዩሮ ስታዲየም በጊዜው ባለመጠናቀቁና አየርላንድ ደግሞ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ደጋፊዎች ስታዲየም ገብተው ጨዋታዎችን እንዲከታተሉ የማድረግ ዋስትናን ባለመስጠቷ ከአስተናጋጅነት ውጪ መሆናቸውን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በወቅቱ ገልጿል።

እ.አ.አ በ2016 በፈረንሳይ በተካሄደው 15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ የነበረችው ፖርቹጋል በጥሎ ማለፉ በቤልጂየም ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ መሆኗ ያልተጠበቀ ውጤት ነበር።

90 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ዌምብሌይ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ጣልያን እንግሊዝን በመለያ ምት በማሸነፍ ታሪካዊውን ዋንጫ አንስታለች። 

በውድድሩ 24 አገራት በስድስት ምድቦች ተከፍለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።

16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (ቫር) ጥቅም ላይ የዋለበት ነው።

ከዚህ ቀደም ከሁለት አገራት በላይ በጣምራ ያዘጋጁት አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ2007 የተካሄደው 14ኛው የእስያ ዋንጫ ነው።

ኢንዶኔዢያ፣ ማሌዢያ፣ ታይላንድና ቬትናም ውድድሩን ያዘጋጁ አገራት ናቸው።

ከዚህ በኋላ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች የ11 አጋራትን ጣምራ አዘጋጅነት ክብረ ወሰንን ያልፉ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ቀጣይ ጊዜያት ምላሽ ይሰጣሉ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም