በአማራ ክልል 84 የገበያ መረጃ ማዕከላት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል-የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 84 የገበያ መረጃ ማዕከላት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል-የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ
ጎንደር ፤ሰኔ 13/2016 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል አምራቹን፣ ሸማቹንና ነጋዴውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በቴክኖሎጂ የተደገፉ 84 የገበያ መረጃ ማዕከላት ወደሥራ መግባታቸውን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
"የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋትና በተዋናዮች መካከል ትስስር በመፍጠር የተሳለጠ ግብይት እንገነባለን" በሚል መሪ ሃሳብ ለጅምላ ነጋዴዎች እና ለሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት የተዘጋጀ ስልጠና በጎንደር ከተማ ዛሬ ተሰጥቷል።
የቢሮው ሃላፊው ዶክተር ኢብራሂም መሃመድ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ የንግድ ልውውጥና የተዋናዮች ትስስር በመፍጠር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተደራጁ የገበያ መረጃ ማዕከላትን ወደስራ በማስገባት ዘመናዊ የግብይት ስርአትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከላቱ የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርት የት እንዳለ፣ በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጥ እና ጥራቱን ለይተው ለሸማቹና ለነጋዴው መረጃን በፍጥነት እንደሚያደርሱ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ጤናማ የግብይት ስርአት እንዲሰፍንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለማስወገድ አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ሃላፊው፣ በቀጣይ ዓመትም 100 የገበያ መረጃ ማዕከላት ወደስራ ይገባሉ ብለዋል።
የስልጠናው ዓላማም የገበያ ተዋናዮችን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ ለዘመናዊ ግብይት መጎልበት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።
የጎንደር ከተማ ባቋቋመው የገበያ መረጃ ማዕከል የምርቶችን ዋጋ መረጃ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ናቸው።
ማዕከሉን ለማዘመንና አዳዲስ አሰራሮችን ለማካተት እንዲቻል ከጎንደር ዩኒቨርሰቲ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር ጸሐፊ አቶ ፍስሃ አዳነ ማህበሩ ከማዕከሉ በሚያገኘው መረጃ መሰረት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ዋጋና መገኛ ቦታ ለአባላቱ እያቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።
በስልጠናው ላይ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከማዕከላዊና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ከጎንደር ከተማ የተውጣጡ ጅምላ ነጋዴዎችና የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት አመራሮች ተሳትፈዋል።