ቀጥታ፡

የብሪክስ አባል አገራት መድረክ የኢትዮጵያ የአዲሱ ብሪክስ ልማት ባንክ አባልነት ጥያቄ እንዲፋጠን ድጋፍ የተገኘበት ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦ በሩሲያ የተካሄደው የብሪክስ አባል አገራት መድረክ የኢትዮጵያ የአዲሱ የብሪክስ ልማት ባንክ አባልነት ጥያቄ እንዲፋጠን ድጋፍ የተገኘበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ፤ በሳምንቱ የተከናወኑ ዐበይት የዲፕሎማሲ ተግባራትንና ቀጣይ ስራዎችን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ በሩሲያ በተካሄዱ የብሪክስ አባል ሀገራት ብሔራዊ ተወካዮች እና በ3ኛው የጥምረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአባል አገራት ስብሰባ ላይ ስኬታማ ተሳትፎ አድርጋለች ብለዋል።

በብሔራዊ ባንክ ገዥ እና በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ማሞ ምህረቱ፤ የሚመራ ልዑክ በብሪክስ አባል ሀገራት ብሔራዊ ተወካዮች፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በ3ኛው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አባል ሀገራት መድረኮች ላይ ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፤ በ3ኛው የብሪክስ የአባል አገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በብሪክስ ጥምረት ያላትን የጎላ ሚና ለማሳደግ የወሰደቻቸውን እርምጃዎች አብራርተዋል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ወቅታዊና አንገብጋቢ ድንበር ዘለል ጉዳዮች ላይ የጂኦ-ፖለቲካል ውጥረት ላይ እውነተኛ የዓለም አቀፋዊ ትብብርና አጋርነት የግድ እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውን አንስተዋል።

የብሪክስ ጥምረት በተለዋዋጭና ሊተነበይ በማይቻል የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚክ ምኅዳር ተግዳሮትን በአጋርነት ለመቅረፍ አረጋጊ ኃይል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

በመድረኮቹ የታዳጊ አገራት ፍትሕዊ የልማት ተጠቃሚነት፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻያያና ተያያዥ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጉዳዮች መዳሰሳቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፤ ከ8 አባል ሀገራትና ተጋባዥ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስኬታማ ምክክር አድርገዋል ብለዋል። 

ይህ  ውይይት ኢትዮጵያ የአዲሱ የብሪክስ ልማት ባንክ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ እንዲፋጠን ድጋፍ የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል።

”የጋራ ሀብቶች ለጋራ እጣፋንታና ብልፅግና፡ የአባይ ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ለትብብርና ቀጣናዊ ውህደት” በሚል መሪ ሃሳብ 3ኛው ስኬታማ ዓመታዊ የቀጣናዊ ውህደትና የአባይ ወንዝ ምክንያታዊ አጠቃቀም መድረክ (AFRIRUN) በአዲስ አበባ መካሄዱንም ገልጸዋል። 

በሳምንቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተለያዩ ሀገራት የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ አምባሳደሮች ጋር የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ምክክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም