የፓስፖርት እድሳት አገልግሎት በክልሉ መጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪ ታድጎናል -የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች

መቀሌ፤ ሰኔ 13/ 2016 ( ኢዜአ)-በትግራይ ክልል የፓስፖርት እድሳት አገልግሎት መጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪ እንደታደጋቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ፖስፖርት የማደስ አገልግሎት ከሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።

የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የተለያዩ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከወራት በፊት ከትግራይ ክልል ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ''በትግራይ ክልል ሰላም እና ልማትን ለማስገኘት ያለን ቁርጠኝነት ሁልጊዜም ፅኑ ነው'' ሲሉ አንስተው ነበር።

በክልሉ የፌዴራል መንግስት አቅም በፈቀደ ልክ አገልግሎቶችን ለማስቀጠልም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም መናገራቸው ይታወሳል።

በቅርቡም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል አጼ ዮሃንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ዳግም በረራ ጀምሯል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም ፓስፖርት ማደስ፣ የጠፋ ፓስፖርት መተካት እና የተበላሸ ወይ እርማት የመስጠት አገልግሎት መጀመሩን ነው የገለጸው።

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ፓስፖርት እያሳደሱ ያገኘናቸው ተገልጋዮች "አገልግሎቱ በመጀመሩ ካላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ወጥተናል" ብለዋል።

ተገልጋዮቹ ከዚህ ቀደም ፓስፖርት ለማሳደስ አዲስ አበባ ድረስ በመጓዝ ከፍተኛ ወጪ ሲያወጡ መቆየታቸውን ገልጸው፤ የአገልግለቱ መጀመር ችግሩን እንዳቃለለላቸው አመልክተዋል።

ከተገልጋዮች መካከል የመቀሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ገብሩ ግደይ፣ አሁን ላይ አገልግሎቱን በቅርበት ማግኘታቸው እንግልትና ወጪ ስላስቀረላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ወጣት ሀዱሽ አብረሃም፣ የፓስፖርት እድሳት አገልግሎት መጀመሩ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቅሶ፤ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የተጀመረው አገልግሎት እንዲጠናከር ጠይቋል።

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ምትኩ ታከለ በበኩላቸው፤ ጽህፈት ቤቱ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉትን ቁሳቁሶች አሟልቶ የፓስፖርት ማደስ ስራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

''ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችሉ የውስጥ ቁሳቁሶች ተሟልቶ ፓስፖርት የማደስ አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን'' ብለዋል።

''አገልግሎት መስጠት በመጀመራችን ደስ ብሎናል'' ያሉት ደግሞ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሰራተኛ ወጣት መአዛ ተክለገሪማ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም