በ13 የመንግስት ተቋማት የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት የሙከራ ትግበራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦በተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀም የሚባክነውን ሃብት ለመቆጣጠር የሚያስችል የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት በ13 የመንግስት ተቋማት የሙከራ ትግበራ ተጀመረ።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት (e-Fleet Management) የሙከራ ትግበራ ከሚደረግባቸው 13 የፌዴራል መንግስት ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል።

ኢ-ፍሊት ማኔጅመንት ማለት ክንውኖችን በጥራት፣ በብቃት፣ በሰዓት እና በበጀት መጥኖ መፈፀም የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ስርአት ነው። 

በተለይም የተሽከርካሪ ንብረት አጠቃቀም፣ አያያዝ፣ የግዥ ሂደትና አወጋገድን በተመለከተ የላቀ ጠቀሜታ ያለው የአሰራርና ቁጥጥር ስርአት መሆኑ ይነገርለታል።

በመሆኑም የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀም የሚባክነውን ሃብት ለመቆጣጠር በ13 የመንግስት ተቋማት የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት የሙከራ ትግበራ ጀምሯል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ፤ በመንግስት ተቋማት በግዥና ንብረት የሚስተዋለውን ሙስና እና ብልሹ አሰራር ለመከላከል የሚያስችሉ አሰራሮች በመተግበር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ሲባል የዲጂታል ስርዓት በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በ160 የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ተግባራዊ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀም የሚባክነውን ሃብት ለመቆጣጠር የሚያስችል የኢ-ፍሊት ማኔጅመንት በ13 የመንግስት ተቋማት የሙከራ ትግበራ ተጀምሯል ብለዋል

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የለማው የኢ-ፍሊት ማኔጅመት መተግበሪያ የተሽከርካሪ ሥምሪትና አጠቃቀምን ከማሻሻል ባለፈ የሃብት ብክነትን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ መተግበሪያ ተሸከርካሪው ያለበትን ቦታ የማመላከት፣ ከተሽከርካሪ ጥገና እና ነዳጅ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን መከታተል የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ኢ-ፍሊት በቀጣይ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የሙከራ ትግበራ ከሚደረግባቸው ተቋማት መካከል የገንዘብ ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር የሚጠቀሱ ሲሆን የየዘርፉ ሃላፊዎች የዲጅታል አሰራሩ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስቴር የስራ አመራር ስራ አስፈፃሚ ግዛው ኃይሉ፤ ኢ-ፍሊት ከተሽከርካሪ ጥገና እና ነዳጅ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የመሰረታዊ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ግዛቸው አሰግድ በበኩላቸው፤ ለግልጽ አሰራርና የሃብት ክትትል መተግበሪያው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአሰራሩ ውጤታማነትም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚዎቹ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም