የአገር መከላከያ ሠራዊት ያስመዘገበውን ከፍ ያለ ዝና ተመራቂ መሰረታዊ ወታደሮችም ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ሃላፊነት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአገር መከላከያ ሠራዊት ያስመዘገበውን ከፍ ያለ ዝና ተመራቂ መሰረታዊ ወታደሮችም ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ሃላፊነት አለባቸው

ሁርሶ ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦ የአገር መከላከያ ሠራዊት በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በታላቅ ወታደራዊ ስነ ምግባር በመወጣት ያስመዘገበውን ከፍ ያለ ዝና ተመራቂ መሰረታዊ ወታደሮችም ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ሃላፊነት እንዳለባቸው ሌተናል ጄኔራል ሀጫሉ ሸለመ አስታወቁ።
በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለስምንተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች ዛሬ አስመርቋል።
በመከላከያ ህብረት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ በምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የስራ መመሪያ ሲሰጡ እንደተናገሩት፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገር ሉዓላዊነት የማስጠበቅና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተግባሩን በብቃት የሚፈጽም ነው።
ዛሬ በሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁት መሠረታዊ ወታደሮች በቀሰሙት ዕውቀት በመታገዝ የአገርን ሰላም የመጠበቅና ሉዓላዊነት የማስከበር ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ አሳስበዋል ።
በቀጣይም የተሻለ የሙያ ብቃትና ደረጃ ላይ ለመድረስ ከሌሎች በተግባር እየተማሩ መሄድ እንዳለባቸው ገልፀው፤ ይህም የአገርን ከፍታና ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል።
እንደ ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ገለፃ የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተልዕኮ በብቃትና በታላቅ ወታደራዊ ስነምግባር በመወጣት ከፍ ያለ ዝና አትርፏል ።
ተመራቂዎቹ ይህንን ዝና የመጠበቅና ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ኃላፊነት እንዳለባቸው በማስገንዘብ።
በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲንጀት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ በበኩላቸው፤ አዲሱ ትውልድ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ወደ ውትድርና ሙያ በስፋት እየተቀላቀለ ይገኛል።
የዛሬ ተመራቂዎችም የዚህ ወጣት ትውልድ አባላት መሆናቸውን ገልፀው፤ አገራቸውን ከፀረ ሰላም እና ከፀረ ልማት ሃይሎች በብቃትና በታታሪነት በመጠበቅ የራሳቸውን አሻራ እንደሚተክሉ አረጋግጠዋል።
ኮሎኔል አዲሱ አክለውም የስምንተኛ ዙር ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች በቆይታቸው የቀሰሙት ዕውቀትና ጥበብ ከነባሩ ሰራዊት ጋር ተቀላቅለው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችላቸው ነው።
የስምንተኛ ዙር ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በተለያዩ ተግባራዊ ትዕይንቶች ለዕለቱ የክብር እንግዳ እና ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች አሳይተዋል።
ተመራቂዎቹ እንዳሉት የአገራቸውን ዳር ድንበርና ዘላቂ ሰላም በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ አስፈላጊውን መስዕዋትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ ሌተናል ጄነራል አጫሉ እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ፣ በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎችና ለተቋማት የተዘጋጁትን እውቅናና ሽልማት አበርክተዋል።