ቀጥታ፡

በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የተሳካ የዲፕሎማሲ ስራ ተከናውኗል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦ በሩሲያ በተካሄደው ሶስተኛው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራ መከናወኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ፤ በሳምንቱ የተከናወኑ ዐበይት የዲፕሎማሲ ተግባራትንና ቀጣይ ስራዎችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በሩሲያ በተካሄደው 3ኛው የብሪክስ የአባል ሀገራት ስብሰባ ላይ መሳተፏን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ በብሔራዊ ባንክ ገዥ እና በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ማሞ ምህረቱ የሚመራ ልዑክ በሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራ ሰርቷል ብለዋል።

በሦስተኛው የብሪክስ የአባል ሀገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ በተለዋዋጭ እና ሊተነበይ በማይቻል የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚክ ምኅዳር ውስጥ ብሪክስ ሀገራትንና ሃብቶችን በማሰባሰብ ዓለም አቀፍ ተግዳሮትን በአጋርነት ለመቅረፍ አረጋጊ ኃይል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ኢትዮጵያ አጽንኦት ሰጥታለች ብለዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና ሌሎች መስኮች የኢኮኖሚ ግንኙነት በማሳደግ የልማት ፋይናንስን በመጨመር የአካታች እና ዘላቂ ልማትን መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነም መልዕክት መተላለፉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ተሳትፎ የጎላ ሚና መወጣት እንደምትችል ገለፃ ተደርጓል፣ ዕውነተኛ ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

የታዳጊ ሀገራትን ፍትሕዊ የልማት ተጠቃሚነት ድጋፍ፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻያያና ተያያዥ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጉዳዮች መዳሰሳቸውንም ጠቅሰዋል።

ከብሪክስ ስብሰባ በተጓዳኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፤ ከ8 አባል ሀገራትና ተጋባዥ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ምክክር መደረጉን አንስተዋል።

በዚህም ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ኢትዮጵያ በስትራቴጂክ ትብብር የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል ስኬታማ ምክክር ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በውይይቶቹም ኢትዮጵያ የአዲሱ የብሪክስ ልማት ባንክ አባል እንድትሆን የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን ማረጋገጫ እንደሰጡ አንስተዋል።

በአጠቃላይ በሩሲያ በተካሄደው 3ኛው የብሪክስ የአባል ሀገራት ስብሰባ ኢትዮጵያ የብሪክስ ማዕቀፍ ጥምረት ንቁ ተዋናይ እየሆኑ ከመጡ ሀገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች ብለዋል።

“የጋራ ሀብቶች ለጋራ እጣፋንታና ብልፅግና፡ የአባይ ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ለትብብርና ቀጣናዊ ውህደት” በሚል መሪ ሃሳብ ሦስተኛው ዓመታዊ የቀጣናዊ ውህደት እና የአባይ ወንዝ ምክንያታዊ አጠቃቀም መድረክ (AFRIRUN) በአዲስ አበባ መካሄዱንም ገልጸዋል።

በሳምንቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተለያዩ ሀገራት የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ አምባሳደሮች ጋር የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ምክክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም