ቀጥታ፡

የ87 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየወሰዱ ነው

ጂንካ ፤ ሰኔ 13/2016(ኢዜአ)፦ ከግብርና ስራዬ በተጓዳኝ መደበኛ ትምህርቴን ለመከታተል ወስኛለሁ  ይላሉ የ87 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው የ6ኛ ክፍል ተፈታኙ  አዛውንት።

በአሪ ዞን በደቡብ አሪ ወረዳ ቲኪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት የ87 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ ማሞ ገንገርሺ የ6ኛ ክፍል ፈተናቸውን እየወሰዱ ነው።

የ87 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ማሞ የ16 ልጆች አባት ሲሆኑ 38 የልጅ ልጆችን አፍርተዋል።

ከ38 የልጅ ልጆቻቸው 7ቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ከፍተኛ ትምህርት የተቀላቀሉ ሲሆን ሁለቱን ደግሞ በድግሪና በዲፕሎማ አስመርቀዋል።

"ልጆቼን ሳስተምር የመማር እድል አላገኘሁም" ያሉት አቶ ማሞ፤"አሁን ልጆቼ ጥሩ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በግማሽ ቀን የግብርና ስራዬን፣ በግማሽ ቀን ደግሞ መደበኛ ትምህርቴን ለመከታተል ወስኛለሁ" ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናቸውን እየወሰዱ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ማሞ፤ ውጤታማ ለመሆን በማሰብ አስቀድመው ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልዋል።

"ትምህርት የህይወት ዑደት አንዱ አካል ነው" ያሉት  የዕድሜ ባለፀጋው "ሁሉም ሰው በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ቢገኝ ከመማር ወደ ኋላ ማለት የለበትም " ሲሉ መክረዋል። 

ዕድሜዬ እስከፈቀደ ድረስ ትምህርቴን አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ሲሉም አዛውንቱ   አክለዋል።

"አሁን ላይ ሁሉም ነገር ቴክኖሎጂ ይፈልጋል፤ እኔ የተሰማራሁበት የግብርና ስራ ሳይቀር ሁሉም የስራ መስኮች እንደከዚህ ቀደሙ በልምድ ብቻ የሚከወኑ አይሆኑም " ብለዋል።

"በመሆኑም ማንኛውንም ስራ ለማከናወን ቴክኖሎጂን መጠቀም እና የካበተ ዕውቀት መያዝ አስፈላጊና ግዴታ በመሆኑ ቀሪ የዕድሜ ዘመኔን በመማርና አዳዲስ ዕውቀቶችን በመሸመት ለማሳለፍ ወስኛለሁ " ሲሉ ተናግረዋል።

የቲኪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኪኪጆ ግቅሺ፤ አዛውንቱ በትምህርት ቤቱ በሰዓት አክባሪነታቸውና ለትምህርታቸው በሚሰጡት ትኩረት ለትምህርት ቤቱ አርአያ ናቸው ብለዋል።

በትምህርታቸውም ጥሩ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው ከ 1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ በመውጣት ጥንካሬያቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

የአሪ ዞን ዋና  አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ የ6ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኙ አባት አስደናቂና ለትውልዱ አርአያ የሚሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

"አዛውንቱ ተስፋ አለመቁረጥን፣ ለአላማ መኖርንና ጽናት አስተምረውናል" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ሁሉም ሰው ከእኚህ አባት በመማር በተሰማራበት የስራ መስክና ባለበት የትምህርት ደረጃ ውጤታማ ለመሆን መትጋት አለበት ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ አመት 100 ሺህ 507  የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም