ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ተጠቅሞ ፈጣን ዕድገትና ልማት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ ነው - አቶ ጥላሁን ከበደ

ሶዶ ፤ ሰኔ 12/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉትን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች  በመጠቀም ፈጣን ዕድገትና ልማት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

"ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንፍጠር፤አምራቿንና ምርታማዋን ደቡብ ኢትዮጵያ እውን እናድርግ!" በሚል መሪ ሀሳብ ክልል አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ያለውን ፀጋና እምቅ አቅም ለይቶ በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን የመሳብ ስራ እየተሰራ ነው።

በዚህም ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የክልሉን ልማት ለማፋጠን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

ክልሉ የተፈጥሮ ሀብቱን ጨምሮ ያሉትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ፈጣን ዕድገትና ልማት ማስመዝገብ እንደሚችልም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም ለበርካታ ሥራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በጋራ ተቀናጅቶ መስራት ይገባልም ብለዋል። 

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኦንጋዬ ኦዳ በበኩላቸው የክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ  ለባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግና ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በዚህም በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም ክልሉን ለማልማትና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በክልሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ በተለይ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በማዕድን ዘርፎች ባለሀብቶችን በማሰማራት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። 

በክልሉ ያሉትን አማራጮች በአግባቡ በማስተዋወቅና በማበረታታት ዘርፉ እንዲጎለብት ከመስራት በተጨማሪ፣ ቦታ ወስደው በገቡት ውል መሠረት በማያለሙ አካላት ላይ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ከ38 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 1 ሺህ 581 ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች መሰማራታቸውን ገልጸው፣ በዚህም ከ125 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን  አስታውቀዋል። 

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በዞኑ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 518 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። 


 

በዚህም ከ38 ሺህ በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን  አመላክተዋል።

የዞኑ አስተዳደር  ወደ ዞኑ መጥተው  ለሚያለሙ  ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል። 

በፎረሙ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር የተደረገ ሲሆን፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የተረከቡትን ቦታ በአግባቡ ያለሙ ባለሀብቶች ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም